🚩 የወልድ ዘላለማዊ ውልደት በብሉይ ኪዳን (ክፍል 1)
🚩 The Eternal Begetting of The Son in The Old Testament (Part 1)
በመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮና በታሪካዊው ክርስትና ውስጥ የወልድ ዘላለማዊ ውልደት አስተምህሮ ወይም The Eternal Begetting of The Son የሚባል አስተምህሮ አለ። እርሱም ምንድነው ወልድ በዘላለማዊ ውልደት ከአብ ተወልዷል የሚለው አስተምህሮ ነው። ወልድ ዘላለማዊ እንጂ ጊዜያዊ ባልሆነ፥ መንፈሳዊ እንጂ ቁሳዊ ባልሆነ፥ ያን አንዱን መለኮታዊ ባህርይ ባለያየ ውልደት ከአብ ተወልዷል። ወልድ የአብ ዘላለማዊ ልጅ የሆነው ከዚህ ዘላለማዊ ወልደት የተነሳ ነው። ቀጥለን እንደምንመለከተው ይህ አስተምህሮ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሲሆን ከመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በነበሩ ክርስቲያኖች ዘንድ የታመነ ነው።
ለምሳሌ ከአብያተክርስቲያናት መከፋፈል በፊት በነበረችው በአንዲቷ ቤተክርስቲያን በተካሄደው የኒቂያ ጉባዔ የእምነት መግለጫ ወይም The Nicene Creed ላይ "..begotten of the Father before all ages.." ወይም "..ከዘመናት ሁሉ በፊት ከአብ የተወለደ.." ይላል። ቀጠል አድርጎም "..begotten not created.." ወይም "..የተወለደ እንጂ ያልተፈጠረ.." ይላል። እነዚህ ሀረጎች በሙሉ ወልድ ከአብ የተወለደበትን ዘላለማዊ ውልደቱን የሚያመለክቱ ናቸው። ስለዚህ ይህ ትምህርት በአንዲቱ ቤተክርስቲያን ይታመን የነበረው ጥንታዊው የክርስትና ትምህርት መሆኑን ያሳያል።
ከጉባዔውም ባሻገር ከአብያተክርስቲያናት መከፋፈል በፊት የነበሩ የቤተክርስቲያን አባቶች እና አብያተክርስቲያናቱ ከተከፋፈሉ በኋላ የመጡት የሁሉም አብያተክርስቲያናት አባቶች ያስተማሩት ትምህርት ነው። ይህን በስፋት መመልከት የሚቻል ሲሆን ለናሙና ያህል ከክፍፍሉ በፊት የነበሩ ሶስት የቤተክርስቲያን አባቶች በዚህ ጉዳይ ምን እንዳሉ እንመልከት፦
1) St. Athanasius (296 AD - 373 AD)
"..We understand in like manner that The Son is #begotten not from without but #from_The_Father.." (Discourse against the Arians, Discourse 2:33)
1) ቅዱስ አትናቴዎስ (296 AD - 373 AD)
"..እኛም በዚሁ መንገድ ወልድ ከውጪ [ከአንዱ መለኮታዊ ባህርይ ውጪ] ሳይሆን #ከአብ_እንደተወለደ እንረዳለን.." (ጸረ አርዮሳውያን ስብከት; ስብከት 2:33)
ከ451 የቤተክርስቲያን መከፋፈል በፊት በነበረችው አንዲቱ ቤተክርስቲያን ውስጥ የነበረው እውቁ የቤተክርስቲያን አባት ቅዱስ አትናቴዎስ ወልድ ከአብ መወለዱን የአርዮሳውያንን የስህተት ትምህርት በመቃወም በጻፈው ስብከቱ ላይ እንዲህ ገልጿል። ይህ ወልድ በዘላለማዊ ውልደት ከአብ ተወልዷል የሚለው ትምህርት በጥንታዊው ክርስትና ይታመን እንደነበር ያሳያል።
2) St. Cyril of Jerusalem (315 AD - 386 AD)
"..God is a spirit, his generation is spiritual: for bodies beget bodies, and for the generation of bodies time needs must intervene, but time intervenes not in #the_generation_of_The_Son_from_The_Father. And in our case what is begotten is begotten imperfect. but #The_Son_of_God_was_begotten_perfect; For what he is now, that is He also from the beginning, #begotten_without_a_beginning" (Catechetical Lecture 11:7)
2) ቅዱስ ቄርሎስ ዘኢየሩሳሌም (315 AD - 386 AD)
"..እግዚአብሔር መንፈስ ነው ስለዚህ ወላዲነቱ መንፈሳዊ ነው። ሰውነት የሚወልደው ሰውነትን ነው። ለሰውነት ውልደት ደግሞ የጊዜ ጣልቃ ገብነት የግድ አለ። #ወልድ_ከአብ_በተወለደበት_ውልደት ግን የጊዜ ጣልቃ ገብነት የለም። ለእኛ [ለሰዎች] ሲሆን ተወላዲው የሚወለደው ፍጹም ሆኖ አይደለም። #የእግዚአብሔር_ልጅ_ግን_የተወለደው_ፍጹም_ሆኖ_ነው። አሁን የሆነውን ነገር ከመጀመሪያውም ነበር፥ #የተወለደውም_ያለ_ጅማሬ_ነው" (ለአዲስ ክርስቲያኖች የተሰጠ ትምህርት 11:7)
ከአራተኛው ክፍለ ዘመን የአብያተክርስቲያናት መከፋፈል በፊት የነበረው ሌላኛው የቤተክርስቲያን አባት ቅዱስ ቄርሎስ ዘኢየሩሳሌም ወልድ ጅማሬ በሌለው፥ መንፈሳዊ በሆነ፥ ፍጹም (perfect) ውልደት ከአብ እንደተወለደ ገና ላልተጠመቁ ግን ወደ ክርስትና ለመጡ ሰዎች ባስተማረው ትምህርት ላይ ገልጾ እንመለከታለን። ይህ ወልድ በዘላለማዊ ውልደት ከአብ ተወልዷል የሚለው ትምህርት በጥንታዊው ክርስትና ይታመን እንደነበር ያሳያል።
3) Novatian (200 AD - 258 AD)
"..Therefore, Christ is both Lord and God, who was not otherwise seen by Abraham, except that as God the Word, #He_was_begotten_of_God_the_Father before Abraham himself" (On The Trinity, 18)
3) ኖቬሽን (200 AD - 258 AD)
"..ስለዚህ ክርስቶስ ጌታም አምላክም ነው፥ ለአብርሃምም እግዚአብሔር ቃልን ሆኖ እንጂ አልታየውም። ከአብርሃም በፊትም #ከእግዚአብሔር_አብ_ተወልዶ_ነበር" (በእንተ ሥላሴ፥ 18)
ይህም የቤተክርስቲያን አባት ከ451 የአብያተክርስቲያናት መከፋፈል በፊት የነበረ የቤተክርስቲያን አባት ሲሆን ወልድ አብርሃም ከመፈጠሩ በፊት እንኳን ከአብ እንደተወለደ ስለ ሥላሴ ባብራራበት መጽሐፉ ከላይ በምንመለከተው መልኩ አስተምሯል። ይህ ወልድ በዘላለማዊ ውልደት ከአብ ተወልዷል የሚለው ትምህርት በጥንታዊው ክርስትና ይታመን እንደነበር ያሳያል።
✍️ መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ትምህርት የሚያስተምረው የቱ ጋር ነው?
አንዲቷ ቤተክርስቲያን ያካሄደችው ጉባኤ እና ከ451 የአብያተክርስቲያናት መከፋፈል (Schism) በፊት የነበሩ አባቶች በሙሉ መግባባት (consensus) ያስተማሩት ይህ ትምህርት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አለ ወይ ስንል መልሱ አዎ ይሆናል። የእግዚአብሔርን ልጅ ዘላለማዊ ውልደት የሚናገረውን የመጀመሪያውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እንመልከት፦
"አንቺም ቤተ ልሔም ኤፍራታ ሆይ፥ አንቺ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ፤ ከአንቺ ግን #አወጣጡ #ከቀድሞ ጀምሮ #ከዘላለም_የሆነ፥ በእስራኤልም ላይ ገዥ የሚሆን ይወጣልኛል" (ሚክ 5:2)
በዚህ ስፍራ ላይ እግዚአብሔር አምላክ ወደ ፊት በእስራኤል ላይ ገዢ የሚሆን መሲህ እንደሚወጣለት ሲናገር እንመለከታለን። ነገር ግን ይህ ወደ ፊት የሚመጣው መሲህ አወጣጡ ከጥንት ከዘላለም ጀምሮ የሆነ እንደሆነ አምላካችን እግዚአብሔር በዚህ ቦታ ላይ ገልጿል። "ቀድሞ" እና "ዘላለም" የሚሉት የዕብራይስጥ ቃላት "קדם/ቄዴም" እና "עולם/ኦላም" የሚሉት ቃላት ሲሆኑ ዘላለማዊነትን ያመለክታሉ (ዘዳ 33:27 መዝ 93:2) አንድ ላይ ተጫፍረው ሲመጡ ደግሞ ዓለም ከመፈጠሩ በፊት የነበረውን ዘላለማዊ እውነታ ያመለክታሉ (ምሳ 8:23) ስለዚህ ይህ የሚመጣው መሲህ ዘላለማዊ ነው።