ቻይና ተመራማሪዎቿን ለስድስት ወራት ቆይታ ወደ ሕዋ ልትልክ ነው
===============
ቻይና ሦስት የሕዋ ተመራማሪዎቿን ለ6 ወራት ቆይታ ወደ ሕዋ በመላክ በሀገሪቱ የጠፈር ምርምር ጣብያ ላይ ለማሳረፍ እየተዘጋጀች መሆኑ ተዘገበ፡፡ ይህም ተመራማሪዎቹን በሀገሪቱ ታሪክ ሕዋ ላይ ረጅም ጊዜ በመቆየት ቀዳሚዎቹ ያደርጋቸዋል ተብሎለታል፡፡ መጪው ቅዳሜ የሀገሪቱ ሰሜን ምዕራባዊ ክፍል ከሆነው የጎቢ በረሃ ከሚገኘው ጂዩኳን የሳተላይት ማምጠቂያ ጣብያ የሚነሱት ተመራማሪዎቹ ሾንቾ-13 በተባለችው መንኮራኩር አማካኝነት ነው ወደ ሕዋ የሚያመሩት፡፡
ወደ ሕዋ ከሚያመሩት ተመራማሪዎች ውስጥ መንኮራኩሯን የሚያበሯት ዣይ ዚገንግ የተባሉት የ55 ዓመት ጠፈርተኛ ከዚህ ቀደም ስፔስዋክ በማከናወን በታሪክ የመጀመሪያው ቻይናዊነት ክብርን የተቀዳጁ ናቸው፡፡ የ41 ዓመቷ እንስት የሕዋ ተመራማሪ ዋንግ ያፒንግ በበኩላቸው በተልዕኮው ላይ ብቸኛዋ ሴት ሲሆኑ ከዚህ ቀደምም ወደ ቻይና የሙከራ ሕዋ ምርምር ጣብያ ካቀኑት ቀዳሚዎቹ ተመራማሪዎች መካከል ናቸው፡፡ ሌላኛው የጉዞው አካል ዪ ጎንፉ የተባሉት የ41 ዓመት ተመራማሪ ግን ወደ ሕዋ ሲያመሩ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜያቸው ነው፡፡
የቻይና ህዋ ምርምር ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተሩ ሊን ሺጀን በሰጡት መግለጫ መንኮራኩሯንም ሆነ ሌሎች ስራዎችን የተመለከቱ ሙከራና ቅድመ ዝግጅቶች የተጠናቀቁ ሲሆን ተመራማሪዎቹ በሕዋ ላይ ቆይታቸው የሀገሪቱን የጠፈር ምርምር ጣብያ የማስፋፋት ስራ አካል የሆኑ ቁሳቁሶችን እንደሚገጣጥሙና የህክምና ሙከራዎችንም እንደሚያከናውኑ ገልፀዋል፡፡
የቻይና ሕዋ ምርምር ስራን የሚመራው የሀገሪቱ ጦር ኃይል የጠፈር ምርምር ጣብያውን ሙሉ ለሙሉ ለአገልግሎት ብቁ የሚያደርጉ ሰዎችን በቀጣይ ሁለት ዓመታት ውስጥ እየላከ እንደሚቆይ አስታውቋል፡፡ ሾንቾ-13 ታድያ ወደ ጣብያው ለማምራት አምስተኛዋ መንኮራኩር ትሆናለች፡፡ በቀጣይም ሞንቲየን እና ዌሸን የተሰኙ ሁለት አካላት ሾንቾ-14 የተባለችውን መንኮራኩር በተጠቀም ወደ ጣብያው እንደሚላኩ ሲጠበቅ ሁለቱ አካላት ተደምረው የጣብያውን ጠቅላላ ክብደት ወደ 60 ቶን ያደርሱታል፡፡
ነገር ግን የቻይናው ጣብያ ከአውሮፓውያኑ 1998 አንስቶ በስራ ላይ ካለውና 450 ቶን ከሚመዝነው ዓለም አቀፉ የጠፈር ምርምር ጣብያ ጋር ሲነፃጸር አነስተኛ ሊባል የሚችል ነው፡፡ አሜሪካን የቻይናን ሕዋ ምርምር ሚስጥራዊነት እና ከጦር ኃይሉ ጋር ያለውን ትስስር በመጥቀስ ቻይናን በዚህ ዓለም አቀፍ የትብብር ጣብያ ላይ ተሳታፊ እንዳትሆን ማድረጓ ይታወሳል፡፡ ቻይና በበኩሏ እ.አ.አ ከ1990ዎቹ ጅማሮ አንስቶ የራሷን ጠፈር ምርምር ጣብያ ለመገንባት ስትጥር ቆይታለች፡፡ አሁንም ቢሆን በሁለቱ ሀገራት መካከል የሕዋ ምርምር ትብብር መፍጠር ቀላል የማይባል እና በሕግጋት የታጠረ ሆኖ ቢቀጥልም በአንፃሩ ቻይና ከአሜሪካን ውጪ ከአውሮፓውያን ጋር አብራ በመስራት ላይ ትገኛለች፡፡
ሀገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሕዋ ምርምር ስራዋን በፍጥነት እያሳደገች የምትገኝ ሲሆን ከአውሮፓውያኑ 2003 አንስቶም 14 ያህል የሕዋ ተመራማሪዎቿን ወደ ሕዋ ልካለች፡፡ የራሷ በሆነ የጠፈር አካል ላይ ተመራማሪዎቿን በማሳረፍም ከሶቭየት ህብረት እና አሜሪካን ቀጥሎ ሦስተኛዋ ሀገር ናት፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በቅርቡ ለመድረስ አስቸጋሪ ነው ከሚባለው የጨረቃ ክፍል ላይ አለቶችን ይዛ በመምጣት ትልቅ እርምጃን የተራመደችው ቻይና በያዝነው የአውሮፓውያን ዓመትም ቲኤንወን-1 የተባለ አሳሿን ማርስ ላይ አሳርፋ በዚያ ሕይወት ስለመኖሩ ምርመራ እያደረገች ትገኛለች፡፡
ምንጭ፤ አሶሼትድ ፕረስ
ለተጨማሪ፤ https://apnews.com/article/technology-science-business-china-mars-21b73a2b27b84ef1b38d9caba6980911

AP News
China set to send 3 astronauts on longest crewed mission yet
China is preparing to send three astronauts to live on its space station for six months — a new milestone for a program that has advanced rapidly in recent years.
October 14, 2021 1K 2