የተሻሻለው የፌዴራል ታክስ አስተዳደር አዋጅ የማስረዳት ኃላፊነት እና አዲስ ማስረጃ ማቅረብን በተመለከተ ምን ይላል?
ነሐሴ 25/2018 ዓ.ም (የገቢዎች ሚኒስቴር)
በተሻሻለው የፌዴራል ታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1434/2018 አንቀጽ 59 መሰረት ከታክስ ውሳኔ ጋር በተገናኘ በሚደረግ ማናቸውም የታክስ ክርክር ሂደት የታክስ ውሳኔ ትክክል ያለመሆኑን የማስረዳት ኃላፊነትን እና አዲስ ማስረጃ ማቅረብን በተመለከተ የሚከተለውን ይላል፡-
ከታክስ ውሳኔ ጋር በተገናኘ በሚደረግ ማናቸውም የታክስ ክርክር ሂደት የታክስ ውሳኔ ትክክል ያለመሆኑን የማስረዳት ኃላፊነት የታክስ ከፋዩ ነው፡፡
በዚህ አዋጅ መሰረት ቅሬታ፣ ይግባኝ ወይም የውሳኔ ማስተካከያ ጥያቄን የሚያቀርብ ታክስ ከፋይ በታክስ ውሳኔ ወቅት ካቀረበው የተለየ አዲስ ማስረጃን ማቅረብ አይችልም፡፡
ይሁን እንጂ ይህ ድንጋጌ ቢኖርም አዲስ ማስረጃ በቅሬታ፣ ይግባኝ ወይም ስህተትን ለማረም በሚቀርብበት ወቅት ተቀባይነት ሊያገኝ የሚችለው፦
👉 የማስረጃው አለመታየት በታክስ ከፋዩ የታክስ እዳ ላይ ከፍተኛ ጫናን የሚያስከትል ከሆነ፤
👉 ታክስ ከፋዩ ማስረጃውን ያገኘው የታክስ ውሳኔ ማስታወቂያ ከደረሰው በኋላ ከሆነ፤ ወይም
👉 ሰነዱ ያልቀረበው ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ከሆነ፤ ይሆናል፡፡
በዚህ አዋጅ መሰረት “አዲስ ማስረጃ” ማለት የታክስ ውሳኔ ማስታወቂያ ከደረሰው በኋላ በታክስ ከፋዩ የሚቀርብ አዲስ ሰነድ፤ መረጃ፤ ማስረጃ፤ ፍሬ-ነገር ሲሆን፤
👉 በመጀመሪያው የታክስ አወሳሰን ሂደት ለታክስ ባለስልጣኑ ያልቀረበ፤
👉 ለታክስ ውሳኔ ማስታወቂያው ትክክለኛነት አግባብነት ያለው እና መሰረታዊ የሆነ፤ እና
👉 በተወሰነው የታክስ መጠን ወይም በታክስ ከፋዩ ግዴታ ላይ መሰረታዊ ለውጥ የሚያስከትል ነው፡፡

August 31, 2026 5.5K 14