ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ በሐምሌ ወር ብቻ ከ9.19 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ፡፡
ነሐሴ 14/2018 ዓ/ም
በገቢዎች ሚኒስቴር የመካከለኛ ቁ.1 ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በ2019 በጀት ዓመት በሐምሌ ወር ብቻ ቀጥተኛ ከሆኑ ታክሶች፣ ቀጥተኛ ካልሆኑ ታክሶችና ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች ብር 7,876,147,904.21 ለመሰብሰብ አቅዶ ብር 9,191,458,309.18
በመሰብሰብ የእቅዱን 116.7 በመቶ ማሳካት መቻሉን የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ የዕቅድና በጀት አፈፃፀም ክትትል ቡድን አስተባባሪ የሆኑት አቶ ሙሉጌታ አበባው የቅ/ጽ/ቤቱ የማኔጅመንት አባላት ባካሄዱት የ2019 በጀት ዓመት የሐምሌ ወር ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ ወቅት ባቀረቡት ሪፖርት ላይ አመላክተዋል፡፡
አፈፃፀሙ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ክንውን ጋር ሲነፃፀር የብር 3.16 ቢሊዮን ብር ወይም የ52.5 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተገልጿል፡፡
በቀረበው ሪፓርት ላይ የሁሉም የስራ ክፍሎች የሥራ ሂደትና ቡድን አስተባባሪዎች እንዲሁም የየዘርፉ ምክትል ሥራ አስኪያጆች በ2019 በጀት ዓመት በሐምሌ ወር በየስራ ክፍሉ በነበሩ ጠንካራ ጎኖችና በቀጣይ ወር ቢሰሩ የገቢ አፈፃፀሙን ሊያሳድጉ በሚችሉ አንኳር ነጥቦች ዙሪያ ሠፋ ያለ ውይይት ተደርጓል፡፡
የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ስራ አስኪያጅ ተወካይ እና የታክስ ስርዓት ም/ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ እቴነሽ ደሱ ዓመት በ2019 በጀት ዓመት በሐምሌ ወር በፊሲካልም ሆነ በገቢ አሰባሰብ ስራችን አመርቂ ውጤት ያስመዘገብንበት ወቅት በመሆኑ ለዚህ ውጤት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ በየደረጃው ለሚገኙ አመራርና ሠራተኞች እንዲሁም ግብራቸውን በወቅቱ አስታዉቀው ለሚከፍሉ ታማኝ ግብር ከፋዮች ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
ወ/ሮ እቴነሽ አክለዉም የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ እስከፈፃሚ ድረስ ወርዶ እንዲታቀድ ማድረግና የጋራ መግባባት መፍጠር፣ የሥነምግባርን ጉዳይ የሁሉም አጀንዳ እንዲሆን ማድረግና የሥራ ዲሲፒሊንን ማክበር፣ በሁሉም የሥራ ክፍሎች አገልግሎት አሰጣጣችንን በላቀ ሁኔታ ማሻሻልና ቅንጅታዊ አሰራርንን ማሳደግ፣ የኢ-ክሊራንስ አገልግሎት አሰጣጥን ማጠናከር፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ማሻሻልና ሁሉንም ውሳኔዎች በSystem ማውጣት ላይ በትኩረት መስራት፣ በየደረጃው ያለን አመራሮች ኃላፊነታችንን በአግባቡ መወጣትና ድጋፍ ማድረግ፣ በወሩ አፈፃፀም ዝቅተኛ የሆኑ ተግባራትን በመለየት በቀጣይ ወራት የገቢና የፊዚካል ስራዎችን ከእቅድ በላይ ለማሳካት ከወዲሁ አስፈላጊውን ርብርብ ማድረግ እንደሚገባን አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።