የሚያበላ ትምህርት ብቻ ተማሩ
===================
አባትና እና አያት ለልጆቻቸው ያወረሱት እከክ ከሆነ የሚወገደው በረጅም ጥፍር ሳይሆን በብር ነው:: ስለብር ፍቅር ልሰብካችሁ አይደለም:: ምኑ ይሰበካል:: ካፒታሊዝም አሳመነን እኮ:: ዲፕሎማ ወይም ዲግሪ ኖሮኣችሁ ወደ ማጅስቴር ማለቴ ማስትሬት መሄድ ያለባችሁ ማስትሬቱ ብር የሚያመጣ ከሆነ ነው:: ይህንን ስል የምንማረው ለብር ነው እንዴ? የሚል አይጠፋም:: እና ለጽድቅ ነው? ለደሃ PhD እንኳ ቅንጦት ነው:: የሚቆነጥጠው ያጣ ብቻ ነው የሚገባበት:: የአካዳሚ ሰው ካልሆናችሁ ወይም በዶክትሬቱ ብር የማታመጡበት ከሆነ ግን የድህነት ዶክትሬት ነው:: የባጃጅ ሊብሬ ይበልጠዋል:: ባንክ ያውቀዋል:: ኮላተራል ይሆናል:: ገቢዎች የእርጅና ቅናሽ (Depreciation) ይይዝለታል:: ብትሞት ባጃጁ ለልጆችህ ዳቦ ያመጣል::
ማስትሬትህ ወይም ኢንጂነሬትህ ወይም ዶክትሬትህ ግን ባንክ አይዘው, ገቢዎች አያውቀው, ንግድ ቢሮ አይመዝነው:: ንግድ ፈቃድ ልታወጣ ስትሄድ ካፒታል የሚለው ጋር ብር ብቻ ነው የሚሰፍረው:: ንብረት እራሱ በሰርቲፋይድ ገማች የተገመተ ካለ ነው:: ከዚያ ውጭ በእግርህ ብታስብ, በሆድህ ብታስብ አያገባውም:: የባንክ አካውንትህ ስንት እንደሚያነብ ብቻ ነው የምትጠየቀው:: በጣቱ የሚፈርምም በስማርት ቢክ የሚፈርምም ያው ናቸው:: የIT ቆንቋ ካወቅህ ከበቂ በላይ ምሁር ነህ::
Well, ባለህ ብር አገጫጭተህ ዕውቀታዊ ሥራ ለመሥራት say የማደናገር ማለቴ የማማከር ድርጅት ከፈትክ እንበል:: የሆነ ሥራ ስትሠራ ገቢህ 100% ታክስ የሚከፈልበት ገቢ ነው:: ላለፉት 8 ወይም 38 ዓመታት ለትምህርትና ስልጠና ያወጣኸው ወጪ ገቢዎች አያውቀውም:: ባለባጃጁሳ? ህእ! እሱማ ንብረት ነው:: ይቀናነሳል:: ጠበቃዎች ቫት አንመዘገብም, በቁርጥ ነው የምንስተናገደው ብለው ገጅረዋል:: ትክክል ናቸው:: ኢንጂነሪንግ, አካውንቲንግና ማኔጅመንት ኮንሰልታንትም ተመሳሳይ ግጀራ ውስጥ መግባት አለባቸው:: የንግድ ስልጠና ብዙም የማይመስጠኝ ለዚያ ነው:: 10 ሺህ ብር ባስከፍል የመጀመሪያ 5000 ብሩ የገቢዎች ነው:: ቫት እና የትርፍ ግብር 50% ነው ያለብኝ:: በተቀረው አዳራሽ, ሻይ ቡና, ገፋ ካለ ምሳ, የአሰልጣኝ ወጭ ምናምን ሲባል 400 ብር እንኳ አይተርፍም:: 26 ዓመት የተማርኩበትና የ20 ዓመት ልምድ ገቢዎች አያቀናንሰውም::
ለትምህርት ቦታ የሌለውን ሲስተሙን ነው የምነግራችሁ:: በእኔ ጽሑፍ አትፍረዱ:: እንዲህም ሆኖ በትምህርት ተስፋ አልቆርጥም:: ግን የምትሠሩበት ዘርፍ ካላስገደዳችሁ በስተቀር ብር ሳትይዙ ወደ PhD እንዳትሄዱ:: ዶክተር ሆነህ ራበኝ ስትል የመማር ማስተማሩን ሞራል ላይ ነው በረዶ የምትቸልሰው:: ብዙ ብር ሳልይዝ በጁማዓ እንኳ ኮፊያ አላደርግም:: አያምርብኝም:: አዲስ ጫማ አድርጌ የተንሻፈፈ, ጸጉሬን ተከርክሜ የተንጨባረረ ይመስለኛል:: አካውንት ሞላ ሲል በኤርገንዶ ሰርግ ብትሄድ ሊሞዚን ይመስልሃል:: ሱፍ እና ክራባት ማለት የባንክ አካውንት ውስጥ ነው ያለው:: ጫካ የገቡ ሰዎች ለምን ወጥረው እንደሚ^ዋጉ ድሮ ነው የተረዳሗቸው:: ፋብሪካዎቻቸውን ትተው ጫካ የገቡና ያስከበሩ ብዙ አሉ:: እና ወንድሜ መኝታውን ተውና ወደ ቢዝነስ ጫካ ግባ:: ለምን ድንጋይ ጠረባ አይሆንም:: በኢንተርኔት የሚሠራም ሊሆን ይችላል:: ልክ ብሪቱ ስትመጣ በ PhD ተደበር:: ትምህርት ደስ ይላል:: ልጅ የሆንክ ይመስልሃል:: የሚበላው ነገር የሌለው ምእመን የሚያበላ ፊልድ ብቻ ነው መማር ያለበት:: እምቢ ካለ መገረፍ ነው ያለbut! እንዲህ ብጫ ብጫውን ካልተነጋገርን ለውጥ የለም::
ምክንያቱ አንድ እና አንድ ነው:: Capitalism mapped everything to capital. ካፒታሊዝም እያንዳንዱን ነገር ካፒታል (ገንዘብ) ጋር አስተሳስሮታል::