ከ190 በላይ ጠበቆች ገንዘብ ሚኒስቴርን ከሰዋል። • የጥብቅና ሙያ የንግድ ስራ አይደለም፤ የፍትህ አካል ነው? በጠበቆች ላይ የተጫነው የግዴታ የቫት (VAT) ምዝገባ እና የፍትህ ስርአቱ አደጋ!? • የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያዎች (ጠበቆች) በታሪካቸው ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በሙያዊ ነፃነታቸው እና በኢኮኖሚያዊ ህልውናቸው ላይ የመጣባቸውን የተሳሳተ የመንግስት መመሪያ በመቃወም ለፍትህ ቆመዋል። የገንዘብ ሚኒስቴር ያወጣው መመሪያ ቁጥር 1104/2017፣ ማንኛውም ጠበቃ የገቢ መጠኑ ምንም ይሁን ምን ለተጨማሪ እሴት ግብር (VAT) እንዲመዘገብ እና እንደ ማንኛውም የንግድ ድርጅት በየወሩ ሪፖርት እንዲያደርግ ያስገድዳል። ይህ መመሪያ የህግ ባለሙያዎችን መብት ከመጣስ ባለፈ፣ ተራው ዜጋ ፍትህ እንዳያገኝ ትልቅ የገንዘብ እንቅፋት የሚፈጥር በመሆኑ ከ190 በላይ ጠበቆች በጋራ ክስ መስርተዋል። ዋና ዋና የመከራከሪያ ነጥቦች 1. ህገ-ወጥ እና ከአዋጅ ውጪ የሆነ መመሪያ፡- • የቫት አዋጅ ቁጥር 1341/2024 በግልፅ እንደሚደነግገው፣ የቫት ምዝገባ ግዴታ የሚሆነው አመታዊ ገቢያቸው ከ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ለሆኑ ድርጅቶች ብቻ ነው። ሆኖም የገንዘብ ሚኒስቴር ይህንን የአገሪቱን ከፍተኛ ህግ በመጣስ፣ ለጠበቆች ብቻ የተለየና መዳረሻው ዜሮ (Zero Threshold) የሆነ መመሪያ ማውጣቱ "ከስልጣን በላይ" (Ultra Vires) የሆነ ተግባር ነው። 2. ጠበቃ የፍትህ ባለድርሻ እንጂ፣ ነጋዴ አይደለም፣ • የጥብቅና ሙያ በባህሪው የዜጎችን ህገ-መንግስታዊ መብት ለማስከበር የሚቆም እንጂ እንደ ሸቀጥ የሚሸጥና የሚለወጥ ንግድ አይደለም። ጠበቆች ፈቃዳቸውን ለማደስ በየዓመቱ የነፃ የህግ አገልግሎት (Pro Bono) የመስጠት ግዴታ አለባቸው። ይህንን ማህበራዊ ኃላፊነት ያለበትን ሙያ እንደ ተራ የችርቻሮ ንግድ ቆጥሮ ታክስ መጫን የሙያውን ክብር ዝቅ ማድረግ ነው። 3. የዜጎች ፍትህ የማግኘት መብት አደጋ ላይ መውደቅ፡- • በጥብቅና አገልግሎት ላይ 15% ቫት መጫን ማለት፣ ደንበኛው ወይም ተከሳሹ ለፍትህ የሚከፍለው ዋጋ በ 15% ይጨምራል ማለት ነው። ይህ ደግሞ አቅም የሌላቸው ዜጎች በፍርድ ቤት የመከራከር መብታቸውን እንዲተዉ ያስገድዳቸዋል። ፍትህ ለሀብታም ብቻ የሚሸጥ ሸቀጥ መሆን የለበትም። 4. ምክንያታዊ ያልሆነ የወጪ አያያዝ፡- • የጠበቆች ስራ አእምሯዊ እንጂ ግዙፍ ግብዓቶችን (Raw materials) የሚጠቀም አይደለም። በመሆኑም እንደ ነጋዴ "የወጪ ደረሰኝ" (Input VAT) አሰባስቦ ለማቅረብ የሙያው ባህሪ አይፈቅድም። መንግስት ይህንን ከግምት ውስጥ ያላስገባ "ሂሳብ ያዙ" የሚል ትዕዛዝ ማውጣቱ በተግባር ሊተገበር የማይችል እና ሙያውን ለማፈን የታለመ ነው። የፍርድ ቤት ሂደት እና የእግድ ጥያቄ መዘግየት፡- • ጉዳዩ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀረበ ቢሆንም፣ የፍርድ ቤቱ የእግድ ጥያቄውን በተደጋጋሚ መቅጠር እና ውሳኔ አለመስጠት ጠበቆችን እያሳዘነ ይገኛል። እግዱ ሳይሰጥ መመሪያው ስራ ላይ መዋሉ ጠበቆች ፈቃዳቸውን እንዳያድሱ እና ስራቸውን እንዳይሰሩ እያገዳቸው ነው። • ጠበቆች ፍትህ ከዘገየ እንደተነፈገ ይቆጠራል እንደሚባለው፣ ፍርድ ቤቱ የጉዳዩን አሳሳቢነት ተረድቶ በአስቸኳይ እግድ እንዲሰጥ በችሎት ቀርበን ጠይቀን ነገር ግን ችሎቱ ለቀጣይ ወር ቀጠሮ በመስጠት አልፎታል። #የጠበቆች_ጥሪ፡- • አዋጁን የሚቃረነውና የጥብቅና ሙያን ታሳቢ ያላደረገው መመሪያ በአስቸኳይ እንዲሰረዝ ወይም እንዲሻሻል። • የፍትህ አካል የሆኑት ጠበቆች ላይ የሚደርሰው ጫና የፍትህ ስርአቱን እንዳያናጋ የሚመለከተው አካል ጣልቃ እንዲገባ። ይህ የጥቂት ጠበቆች ጥቅም ሳይሆን፣ የሁሉም ዜጋ የፍትህ መብት ጥያቄ መሆኑን ተረድታችሁ ድምፃችንን እንድታስተጋቡልን። ለሙያችን ክብር፣ ለዜጎች ፍትህ በጋራ እንቆማለን‼️🙏 @የሕግ_ጉዳይ #All_Business_Laws_and_Businesses_Free_Service https://t.me/GeezLaws
TelegramGeez Laws Center ግእዝ የሕግ ማእከልwww.geezlaw.com | +251948449999 [email protected] #Free_Services #All_Business_Laws & Businesses
7
2