ስለ ኑዛዜ ከውርስ ሕግና ከሰበር ውሳኔዎች አንፃር! *** የኢትዮጵያ የውርስ ሕግ ኑዛዜ ማለት ምን ማለት… — Geez Laws Center ግእዝ የሕግ ማእከል — TG.ME

ስለ ኑዛዜ ከውርስ ሕግና ከሰበር ውሳኔዎች አንፃር! *** የኢትዮጵያ የውርስ ሕግ ኑዛዜ ማለት ምን ማለት እንደሆነ የሰጠው ትርጉም ባይኖርም አንድ ኑዛዜ ህጋዊ ውጤት እንዲኖረው ማሟላት የሚገባቸውን መስፈርቶች ምን ምን እንደሆኑ በዝርዝር የሚያስቀምጡ የሕግ ድንጋጌዎችን ከፍትሐብሔር ህግ ቁጥር 857 እስከ 908 ተደንግጎ እናገኘዋለን፡፡ በዚህ ጽሁፍ ኑዛዜ በምን አግባብ ቢደረግ በሕግ ዘንድ ውጤት ይኖረዋል፤በውርስ ሕጋችን ላይ የተቀመጡት የኑዛዜ አደራረግ ስርዓቶች አስገዳጅነታቸው እስከምን ድርስ እንደሆነና ኑዛዜ በፍርድ ቤት ቢጸድቅ ሊያስገኝ የሚችለው ውጤትና ባለመጽደቁ የሚያመጣው ተጽእኖ ምን እንደሆነ ከውርስ ሕግ እና አስገጋጅ ከሆኑ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ውሳኔዎች አንጻር በአጭሩ ዳሰሳ ለማድርግ ተሞክሯል፡፡ ለኑዛዜ ዋጋ መኖር አስፈላጊ የሆኑ የስረ ነገር ሁኔታዎች በፍትሐ ብሔር ህግ ከአንቀጽ 857 እስከ 879 የተደነገጉት ድንጋጌዎች ለኑዛዜ ዋጋ መኖር አስፈላጊ የሆኑ የሥረ ነገር ሁኔታዎች (essential condition of wills) አካትተው ተደንግገዋል፡፡ ከእነዚህ አጠቃላይ ደንጋጌዎች ለመረዳት እንደሚቻለው ለኑዛዜ ዋጋ መኖር አስፈላጊ የሆኑ የሥረ ነገር ሁኔታዎች በሁለት ከፍሎ ማየትና መተንተን ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው የኑዛዜ ሁለንተናዊ ወይም ተፈጥሯዊ አስፈላጊ ነገር( inherent or intrinsic elements of will) የሚባለው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በኑዛዜው ይዘት ላይ የሚያተኩርና ለሕግና ሞራል ተቃራኒ መሆን ወይም አለመሆኑን የሚቆጣጠሩ ናቸው፡፡ የኑዛዜ ሁለንተናዊ ወይም ተፈጥሯዊ ነገር የሚባለው ተናዛዡ ኑዛዜውን በሚፈጽምብት ወቅት የነበረው የአእምሮ ሁኔታ ወይም ኑዛዜ የማድረግ ሀሳብ የነበረው መሆኑ( animus testandi ) የምንለው ነው፡፡ የኑዛዜ ክርክር የሚነሳው ኑዛዜ አድርጊው ከሞተ በኋላ ስለሆነ ኑዛዜ አድርጊው በሙሉ ፍላጎቱና ሀሳቡ ኑዛዜውን ያደረገ ስለመሆኑ እንዴት እርግጠኛ መሆን ይቻላል የሚለው ነጥብ ነው፡፡ ይህን ለመረዳት የሚከተሉት ነጥቦች ከግምት ውስጥ መግባት ይኖርባቸዋል፡፡ ሀ) ተናዛዡ ራሱ በሙሉ ሀሳቡ ኑዛዜ የፈጸመ መሆኑ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 857 በተገለጸው መሰረት ሟች ኑዛዜ የማድረግ ሀሰብና ፍላጎት ኖሮት እንደዚሁም የኑዛዜው ይዘት በመረዳት ኑዛዜ ማድረግ ያለበት እሱ ራሱ ብቻ መሆን እንዳለበት በግልጽ ደንግጓል፡፡ ህጉ የሟች ሀሳብ በሌሎች ሰዎች ማለትም በወኪሎች በኩል በኑዛዜ ላይ መግለጽ እንደማይገባው በመከልከል ኑዛዜውን የሟች የግል ስራና የራሱ የሀሰብ መግለጫ መሆን እንዳለበት በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ አንድ ሰው በሌላ ሰው በስሙ ኑዛዜ እንዲያደረግ ፤እንዲለውጥ ወይም እንዲሽር ስልጣን ሊሰጠው እንደማይችል አንድ ሰው ሌላ ሶስተኛ ወገን ወራሹን እንዴት እንደሚወስንና ውርሱ ለማን መተላለፍ እንዳለበት እንዲፈጽም ሊያደርግ እንደማይችል የውርስ ህግ ደነግጋል፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰበር መ/ቁጥር 134836 በቅጽ 22 ላይ በሰጠው አስገዳጅ የህግ ትርጓሜ ላይ እንደተመላከተው “ ኑዛዜ ጥብቅ የሆነ የግል ጠባይ ያለው እና በሟች ብቻ የሚፈጸም በመሆኑ ብዙ ሰዎች አንድ በሆነ ጽሁፋ በጋራ ማናዘዝ የማይቻልና ኑዛዜው ፈራሽ የሚያደርገው ነው፡፡ በመሆኑም በተደረገው ኑዛዜ በሟች የግል ንብረት ላይ ሌላ ሰው ጭምር በአንድ የኑዛዜ ሰነድ ላይ ተናዘው ከተገኙ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 858፤857 እና 880 ተከታዩ ድንጋጌዎች አንጻር ፍርድ ቤቶች ኑዛዜውን ፈራሽ ነው በማለት የሚሰጡት ውሳኔ የሚነቀፍበት ሕጋዊ መክንያት የለም” ሲል የሕግ ትርጓሜ ሰጥቷል፡፡ ለ የተናዛዡ ኑዛዜ የመፈጸም ችሎታ በሁለተኛ ደረጃ የኢትዮጲያ ሕግ የተናዛዡን ኑዛዜ የመፈጸም ሀሳብ (animus testandi) እያለው ኑዛዜ የፈጸመ መሆኑን ለማረጋገጥና ለኑዛዜው ዋጋ ለመስጠት ወይም ላለመስጠት እንደ መስፈርት የያዘው የተናዛዡን ኑዛዜ የመፈጸም ችሎታ (capacity make a will) ነው፡፡ የተናዛዡ ኑዛዜ የመፈጸም ችሎታ የሚመዘነው የተናዛዡ የሚፈጽመው ተግባር ኑዛዜ መሆኑንና የሚፈጽመው ኑዛዜ ይዘት በአግባቡ የሚረዳ መሆኑን ወይም አለመሆኑን በመመዘን ነው፡፡ እዚህ ላይ ግንዛቤ ሊያዝበት የሚገባው ነገር አንድ ሰው በሕግ ችሎታ ያለው መሆኑ አለመሆኑ ጉዳይ ኑዛዜ ለመፈጸም ካለው ችሎታ ጋር በቀጥታ ማይገናኝ መሆኑን ነው፡፡ በሕግ ችሎታ የሌላቸው ሰዎች ኑዛዜ ለመፈጸም ችሎታ ሊኖራቸው ይችላል። ======||===== [email protected] #Free_Services +251948449999 #All_Business_Laws & Businesses https://t.me/GeezLaws

TelegramGeez Laws Center ግእዝ የሕግ ማእከልwww.geezlaw.com | +251948449999 [email protected] #Free_Services #All_Business_Laws & Businesses
❤7
May 4, 2026 2.3K 16