ከዳር ሆነን የፖለቲካውን አቧራና ትርክት ስንታዘብ ብዙ ታዝበን ዝምታን መርጠን ነበር። አንዳንዴ ግን ዝምታ የፍርሃት ወይም የድንዛዜ ምልክት ተደርጎ እንዳይወሰድ፣ አሊያም የሀገርን ሕመም እያዩ አፌን ያዝኩ ለማለት የማይቻሉበት ጊዜ ይመጣል። አዎ... አንዳንዶቹ ጉዳዮች ዝም አይባሉም!
ሰሞኑን ጃዋር መሃመድ «ፅምዶ» በሚል ስለ ተፈጠሩት የኃይል አሰላለፎች የሰጠው ስለታም ትንተና የፖለቲካውን መድረክ ያነቃነቀው እንዲሁ በዋዛ አልነበረም። ከግርግሩ ባሻገር ሰከን ብሎ ላስተዋለው ሰው ግን፣ ይህ ትንተና የአንድ ፖለቲከኛን የውስጥ እድገትና የሀሳብ ጉልምስና በግልጽ የሚያሳይ መስታወት ነው።
ጃዋርን በጎዳና ላይ ተቃውሞዎች፣ በከፍተኛ ማዕበልና በእስር ቤት ውጣ ውረዶች ውስጥ ስናየው ቆይተናል። ዛሬ ግን ያ የትናንቱ የጎዳና ድምፅ፣ ቦታውን ለረጋ፣ ቀድሞ ለሚያይና ስትራቴጂካዊ በሆነ የሀሳብ ምጥቀት ለበሰለ አእምሮ አስረክቧል።
በጋራ ጠላት ጥላቻ ላይ ብቻ ተመስርተው የሚፈጠሩ ጊዜያዊ ጥምረቶች ሀገርን ከጥፋት አያድኑም፤ ይልቁንም አደጋውን ያፋጥኑታል እንጂ። ጃዋር ይህንን እውነት በደፍረት ሲናገር፣ ፖለቲካ ከጊዜያዊ የሥልጣን ጥም ወጥቶ የረጅም ጊዜ የሀገር ደህንነትን መመልከት እንዳለበት እያስገነዘበን ነው። ይህ ደግሞ ከተቃዋሚነት ወደ ሀገር ግንባታ አስተሳሰብ የተደረገ ትልቅ የንቃተ ህሊና ሽግግር ነው።
ፖለቲካ እራሱን እያረመና እያደገ የሚሄድ የታሪክ ህይወት ከሆነ፣ ጃዋር መሃመድ ዛሬ የቆመበት የሀሳብ ማማ የዚያ የብስለት ጉዞው ማሳያ ነው። ያቀረበው ስጋትና የተነተነው አደጋም የፖለቲካውን እውነተኛ መልክ የሚያሳይ ነበር።
#ኢትዮጵያ #ፖለቲካ #ጃዋርመሃመድ #ፅምዶ #ሀገራዊ_አስተሳሰብ
5
1September 4, 2026 646 1