🎁 አቶ ልደቱ አያሌው ፡ ለ ጀዋር መሀመድ የፃፉት ደብደቤ !📨✉️📫
.
.
ግልጽ ደብዳቤ
ለአቶ ጀዋር መሐመድ
ባሉበት፣
ጉዳዩ፦ ማብራሪያ መስጠት እና ጥሪ ማቅረብን ይመለከታል
ሰሞኑን ለንባብ ባበቃሁት መጣጥፍ፣ አንዳንድ ሰዎች የሰሞኑን የታጣቂ ኃይሎች ጥምረት መፍጠር መቃወማችሁ በበቂ አመክንዮ ያልተደገፈ መሆኑን በመግለጽ ለሰጠሁት አስተያየት በፌስ-ቡክ ገጽህ ላይ የሰጠኸውን መልስ አንብቤዋለሁ።
አቶ ጀዋር፣ አንተና እኔ በሀገሪቱ ፖለቲካ የጐላ ተሳትፎ ያለንና አወዛጋቢ በመሆን የምንታወቅ ነን።
ይሁንና እስካሁን ድረስ በምንም ጉዳይ በይፋ ተወዛግበን አናውቅም። ይልቁንም አብረን በታየን ቁጥር ሁለታችንም
ያለ አግባብ የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ ሰለባ ስንሆን ቆይተናል።
በተለይም እኔ፣ ከትግራይና ከኦሮሞ የፖለቲካ ልሂቃን ጋር ተቀራርቤ ለመስራት በማደርገው ሙከራ እስከ ሰባት ዘር-ማንዘሬ ድረስ የግድያ እርምጃ እንዲወሰድብኝ ጭምር ግልጽ ቅስቀሳ ተካሂዶብኛል።
ይህንን ዓይነት ጥረት ሳደርግ የነበረው እንዲሁ ከግል ፍላጐቴ በመነጨ ሳይሆን በአማራ፣ በትግራይና በኦሮሞ የፖለቲካ ልሂቃን መካካል የሚፈጠር መቀራረብ የሀገሪቱን አንድነት ለማጠናከር፣ ሰላም ለማስፈንና የፖለቲካ ባህላችንን ወደ በጐ አቅጣጫ ለመቀየር ከፍተኛ ጥቅም አለው ብዬ ስለማምን ነው። በእኔ በኩል የቱንም ያህል የፕሮፓጋንዳ ጥቃት ቢሰነዘርብን እኔና አንተ ከነልዩነቶቻችን በጋራ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ የመስራት የፖለቲካ ባህል አርዓያ ሆነን እንድንገኝ እንጂ ውዝግብ ውስጥ እንድንገባ ፍላጐት ኖሮኝ አያውቅም።
በዚህም ምክኒያት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከአንተ ጋር በመግባባትና በትብብር ለመስራት ቀዳሚውን ተነሳሽነት ወስጀ ለዓመታት ከፍተኛ ጥረት ሳደርግ ቆይቻለሁ። ይህ እውነት ስለመሆኑም ከማንም በላይ አንተ እራስህ
እንደምትመሰክር አልጠራጠርም።
አሁን ላይ ግን፣ በአንተ በኩል አብሮ ለመስራት ፍላጐት በማጣትህ ምክኒያት ግንኙነታችን ተቋርጧል። በእኔ
በኩል ግንኙነታችንና አብረን መስራታችን እንዲቀጥል አማላጂ በመላክ ጭምር ደጋግሜ ብሞክርም ሳይሳካልኝ ቀርቷል።
በዚህ ምክኒያት በአሁኑ ወቅት በምክክር ወይም በትብብር አብረን እየሰራን ስላልሆነ ልዩነቶች ሲኖሩን በጨዋነት በአደባባይ ጭምር ብንከራከር የሚጠቅም መስሎ ይታየኛል። ምክኒያቱም አሁን ላይ እኔና አንተ፣ የሀገሪቱን ወቅታዊ ፖለቲካ በተመለከተ በጣም በተራራቀ አመለካከት ላይ ነው የምንገኘው።
ከዚህ እሳቤዬ ጋር በተያያዘ ሰሞኑን እኔን በሚመለከት በፌስ-ቡክ ለጻፍከው አስተያየት ብዙ ዝርዝር ውስጥ ሳልገባ የሚከተለውን አስተያየት እሰጣለሁ።
በጽሁፍህ ላይ፣ “ጀዋር የታጣቂ ኃይሎችን ጥምረት እየተቃወመ ነው ” በማለት የተናገርኩት ከተሳሳተ ግንዛቤ
በመነጨ እንደሆነና አንተ ግን የታጣቂዎቹን መተባበር በተመለከተ ድጋፍም ሆነ ተቃውሞ እንደሌለህ አድርገህ
ገልጸሀል። በእኔ እምነት ይህ አስተያየትህ ቅንነትና ሀቀኝነት የጐደለው ነው።
በቅድሚያ ያለበቂ ምክኒያትና መረጃ ሰዎችን በቀላሉ የማልከስ ሰው እንደሆንኩ ትረዳለህ ብዬ እገምታለሁ። እኔ—
“ጀዋር ጥምረቱን እየተቃዎመ ነው” ብዬ የተናገርኩት እንዲሁ በአፍ ወለምታ ወይም አንተ እንዳልከው በግንዛቤ እጥረት ሳይሆን በአግባቡ ተረድቸህ ነው።
እንደ እኔ እና አንተ የፖለቲካ አካሄድን በቀላሉ ለሚረዳ ሰው፣ አንድን ሰው አንድን ነገር ይደግፋል ወይም ይቃወማል? ብለን ለመበየን ከሰውየው አፍ “እደግፋለሁ” ወይም “እቃወማለሁ” የሚሉትን ቃላቶች የግድ መስማት የለብንም። ከተለያዩ ማሳያወች ተነስተን“ ይደግፋል” ወይም “ይቃወማል” ብለን ልንበይን እንችላለን።
ለምሳሌ፣ የወቅቱን የታጣቂዎች ትብብር እንዴት ታዬዋለህ? በሚል ከርዕዮት ሚዲያ ለቀረበልህ ጥያቄ—
“ዐቢይን ለማጥፋት ብዬ ቤቱን አላቃጥልም” በማለት ታጣቂዎቹን ሀገር አፍራሽ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን
ደግሞ ሀገሩን አስቀጣይ አስመስለህ ገልጸሃል። በፌስ-ቡክ ገጽህ ላይም፣ “አገዛዙ በሚፈልገው መልኩ ትብብር
ተብዬዋን ገና ሳትንቀሳቀስ ጐማዋን እየበሳሳት ነው
” በማለት ትብብሩን የሚያናንቅ አስተያዬት ሰጥተሃል።“
ወደ አራት ኪሎ በየት አድርገው ነው የሚመጡት? ህወሓት በአማራ መሬት አልፎ ሊመጣ ነው? ወይስ ፋኖ በኦሮሚያ መሬት አልፎ ሊመጣ ነው?” በማለትም ህወሓትና ፋኖ ወደ አዲስ አበባ የመምጣት መብትና እድል እንደሌላቸው አድርገህ አደገኛና ከፋፋይ አስተያዬት ሰጥተሃል። ይህን በማለትም የትብብሩ አካል የሆነው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት /ኦላ/ ያልተገባ ቅራኔ ውስጥ እንዲገባ ግፊት ለማድረግ ሞክረሃል።
በተጨማሪም ስለ ትብብሩ በይፋ መወራት ከጀመረ በኋላ በፋኖዎችና በአመራሮቻቸው ላይ ግልፅ የሆነ የውንጀላ ክሶችን እያቀረብክ ትገኛለህ።
ይህንን ሁሉ እያደረግህ፣ “ትብብሩን አልተቃዎምኩም” ብትል፣ ቢያንስ እኔን ልታሳምን አትችልም። የፖለቲካ ተንኮልና ሸር በቀላሉ ለሚገባን ሰወች አንተ ጥምረቱን ከመቃወምም ባለፈ ስልታዊ በሆነ አካሄድ ለማደናቀፍ በትጋት እየሰራህ ነው ማለት ይቻላል። እውነቱን ለመናገር ከአንተ አካሄድ ይልቅ የእነ ሻለቃ ዳዊት አቋም የተሻለ ጨዋነት አለው።
እነሱ “ጽምዶን እንቃዎማለን” በማለት የሚያምኑበትን አቋም በግልጽ ነው ያራመዱት። አንተ ግን በቀጥታ “እቃወማለሁ” ብለህ አለመናገርን የፕሮፓጋንዳ ጋሻ አድርገህ እየተጠቀምህ
በተጨባጭ ግን ከመቃወምም ባለፈ ትብብሩን ጥያቄ ላይ የሚጥል ስራ እየሰራህ ነው።
እነዚህ በአደባባይ እያራመድካቸው ያሉ አቋሞችህ ሌላ ተጨማሪ መረጃ ማቅረብ ሳያስፈልግ ትብብሩን በሚመለከት ያለህን አሉታዊ አመለካከት በግልጽ ያሳያሉ።
ነገር ግን ህዝቡ በአደባባይ እየታዘበ ካለው ከዚህ አቋምህም በተጨማሪ፣ በእኔ በኩል—
1ኛ፦ “ጀዋር መሐመድ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ የመሪ እንጂ የመንግስት ለውጥ እንዲመጣ አይፈልግም፣
2ኛ፦ እንኳንስ በትጥቅ ትግል በሰላማዊ መንገድም የፖለቲካ ድርጅቶችና ሲቪክ ማህበራት የብልጽግናውን
አገዛዝ ታግለው ከስልጣን እንዲያወርዱት አይፈልግም፣
3ኛ፦ በተደራጀ የትግል አካሄድም አያምንም፣
4ኛ፦ የወቅቱን የሀገሪቱንና የህዝቡን የህልውና ጥያቄም ወደ የሰላም እጦትና የኢኮኖሚ አቅም መበላለጥ
ጥያቄነት አውርዶ ያየዋል” ብዬ ለመከራከር የሚያስችል ግንዛቤ አለኝ።
ይህ ግንዛቤዬ ስህተት ነው ብለህ የምታምን ከሆነ ፊት ለፊት ተገናኝተን በህዝብ ፊት ልንከራከር እንችላለን። ዝርዝሩን እዚህ ላይ የማልገልጸው የቅራኔያችንን ዙር የበለጠ ማክረር ተገቢ አይሆንም ብዬ ስላመንኩ ነው።
ቢያንስ ግን በዚህ አጋጣሚ፣ ሰላማዊ ህዝባዊ እምቢተኛነት በሀገሪቱ እንዲካሄድ አብረን በጀመርነው የትግል
እንቅስቃሴ ዙሪያ አንድ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ከተሳትፎ እራስህን አግልለህ በግልህ እየሰራህ እንደሆነ፣ በአሁኑ
ወቅት የብዙዎቻችንን የስልክ ጥሪ ጭምር እንደማትመልስ፣ ነገር ግን በትብብር እየሰራህ እንደሆነ አድርገህ እንደምታስመስል ለህዝቡ ማሳዎቅ እዎዳለሁ። በመካከላችን ያሉትን የአስተሳሰብ ልዩነቶች ወደ አደባባይ ከማውጣት ይልቅ በአካል ተገናኝተን ወይም በስልክ ተነጋግረን መፍታት ያልቻልነውም በዚሁ በአንተ እራስን የመነጠል እርምጃ ምክኒያት መሆኑን ህዝቡ ሊያውቀው ይገባል እላለሁ።
አቶ ጀዋር፣ በማንኛውም ጉዳይ ላይ የትኛውንም ዓይነት አቋም ለመያዝ የማንም ፈቃድ አያስፈልግህም።
3September 4, 2026 436 1