በአቪዬሽንና ቴክኒክ ዘርፍ የሚሰጡ ስልጠናዎች የአየር ኃይልን የቴክኖሎጂ አቅም ያሳደጉ ናቸው።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ነሃሴ 27 ቀን 2018 ዓ.ም
በአቪዬሽንና ቴክኒክ ዘርፍ የሚሰጡ የሙያ ማሻሻያ ስልጠናዎች የኢትዮጵያ አየር ኃይልን ዝግጁነትና የቴክኖሎጂ አቅም ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገሩ መሆናቸውን የአየር ኃይል ምክትል አዛዥ ለአየር ኃይል አካዳሚ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን ሌተናል ኮሎኔል ዶክተር ሙሉብርሃን ሀይሉ ገልፀዋል።
የአየር ኃይል አካዳሚ በደረጃ 7 የሙያ ማሻሻያና በአጫጭር የሙያ ዘርፎች ለስድስት ወራት ስልጠና ሲከታተሉ የቆዩ ሰልጣኞችን በሰርተ-ፊኬት አስመርቋል።
በምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው ለተመራቂዎች ሽልማትና ሰርተ-ፊኬት ያበረከቱት ሌተናል ኮሎኔል ዶክተር ሙሉብርሃን ሀይሉ፣ እውቀት በዘመናዊ ቴክኖሎጂና ጥራት ባለው ስልጠና ሲደገፍ የተሰጠንን ማንኛውንም ግዳጅ በብቃት ለመወጣት ያስችላል ብለዋል።
በተለይም በአቪዬሽንና ቴክኒክ ዘርፍ የሚሰጡ የሙያ ማሻሻያ ስልጠናዎች የአየር ኃይሉን የቴክኖሎጂ አቅምና ዝግጁነት ከማሳደግ ባለፈ፣ ተቋሙ ዘመኑን የሚመጥን የሙያ አቅም እንዲገነባ የሚያግዙ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ተመራቂዎችም በስልጠናው ወቅት ያገኙትን ዘመናዊ እውቀትና ክህሎት በተግባር በመተርጎም የተሰጣቸውን ሀገራዊ ኃላፊነት በብቃትና በቁርጠኝነት እንዲወጡ አሳስበዋል።
በዕለቱ የሰልጣኞቹን የስድስት ወራት የስልጠና አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት የአየር ኃይል አካዳሚ የአመራር ኮሌጅ አዛዥ ሌተናል ኮሎኔል አበበ አፋ ናቸው።
ሌተናል ኮሎኔል አበበ በሪፖርታቸው፣ ሰልጣኞቹ በስድስት ወራት የስልጠና ቆይታቸው በንድፈ ሐሳብና በተግባር የታገዘ ትምህርት መከታተላቸውን ገልጸዋል።
ሰልጣኞቹ በተሰጣቸው ትምህርት አመርቂ ውጤት በማስመዝገብ የሙያ ብቃታቸውን ማሳደጋቸውንም ጠቁመዋል። የዘገበው አሰፋ ብርሃኑ ነው
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት
https://dfmc.mod.gov.et/
https://youtube.com/@fdredefenseforce-9629?si=Av-sDKCopw1FfTW2
https://t.me/+E_EOiTY9eq85ODI0
https://www.facebook.com/fdredefense.official
28
12
2September 2, 2026 5.1K 2