ድንግል ማርያም ሀይለ አርያማዊት ናት ወይ?
ይሔ ጥያቄ ከሕጻንነቴ ያደከመኝ ጥያቄ ነው ሞኝ የተከለው እንዲሉ ብዙ ተደጋግሞ ይሰማል ያለምንም በቂ ጥናት ጭፍን ነገር ይዞ አንዴ በታተመ መናፍቃንና ማንነታቸው የምትል መጽሐፍ ምክንያት እስኪሰለቸን ተጠይቀናል እንዳው እንዲት ወዳጄ ይሔንን እስኪሰለችህ ሳትጠየቅ ካቶሊክ መሆንህ አይረጋገጥም ብላ ቀልዳ አስቃኝ ነበር። እስቲ ይሔንን ከዛሬ የተሻለ የምመልስበት ቀን ያለ መስሎ ስላልተሰማኝ እንሂድበት።
1 ድንግል ማርያም ከአዳም ኃጢአት ነጻ ነች ማለት ሰው አይደለችም ማለት አይደለም ኢየሱስ ምንም አይነት ኃጢአት የለበትም ሰው ነው አዳምና ሔዋንም ከውድቀት በፊት ሰው ነበሩ ስለዚህ ይሔንን ጠቅሶ ማንም ሰው አይደለችም እንደምንል አድርጎ ሊያሳይ አይችልም። ምክንያታዊም አይደለም ኢየሱስን ሰው እያሉ እሷ ሰው አይደለችም ብንል ስጋውን ከማን ነሳው ልንል ነው ይሔ የአላዋቂ ክስ ነው።
2 በዛሬው እለት በላቲን ስርዓት የሚከበረው የቅድስት ሐና እና የቅዱስ ኢያቄም የእናትና የአባቷ በዓል ነው ከሰው የተወለደ መቼስ ሰው ነው እና ሰው አይደለችም ትላለችሁ እያሉን ይሔን በዓል የምናከብር መሆናችን የተለየ አለም ከሳሾች መሆናቸው ማሳያ ነው። አከባበራቸው ከምስራቁ ወደ ምዕራቡ የተስፋፋ ሲሆን ቢያንስ ቢያንስ በርግጠኝነት እስከ መካከለኛው ዘመን ድረስ በምዕራቡ አለም አከባበራቸው ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ነበር ለዚህም ከጊዜ በኋላ የመጣ ነው ብሎ ማንም ሊከስ አይችልም ማለት ነው።
3 ቤተክርስቲያን ያለ አዳም ኃጢአት መጸነሷን እና የኃጢአት ዝንባሌ እና ኃጢአት እንደሌለባት ብታስተምርም ይሔ ሰው ከመሆኗ የሚለያት ነገር ነው ማለት አይደለም ሰብአዊ ስሜቶች እድገት ሰብአዊ ውስንነት ነጻነት እና ነጻፍቃዷ ሰብአዊ በሐሪ እንደመያዟ ነው ሙሉ በሙሉ የተጠበቀና ያልተነካ። በጸጋ የሆነላት ነገር ደግሞ ከእግዚአብሔር እንጂ ከራሷ አይደለም። ደግሞም እርሷ ራሷ መድኃኒቴ ብላ እንደጠራችው በልጇ የዳነች የተቤዣት ነች ነገር ግን ከሁሉ ላቅ ባለ መንገድ ለመስቀሉ ቅድመ እይት አስቀድሞ በጸጋ ሞልቷታልና። እንዲሁም ሰው ካልሆነች የአምላክ እናት ተብላ በሰብአዊነት አምላክን ወለደች የሚል ዶግማ ልንይዝ ስለማንችል ይሔ ክስ በኛ ላይ ሊቀርብ ቀርቶ ሊታሰብ አይገባም።
4 ቤተክርስቲያን የማርያምን እናትና አባት ከቀኖናዊ ባልሆኑ ጽሁፎች ስማቸውን የወሰደች ሲሆን ኢያቄም ማለት ያሕዌ ያዘጋጃል ማለት ሲሆን እንዲሁም ሐና ማለት ደግሞ ጸጋ ማለት ነው በዕብራይስጥ።ኢያቄም በቋንቋው ውስጥ ትርጉሙ ከኤሊ እና ከኤሊያቄም ጋር እንደሚተሳሰር እና በተለዋዋጭነት ጥቅም ላይ ውሏል በማለት የሉቃስ ወንጌል የዘር አቆጣጠር ላይ ኢያቄም ነው የተጠቀሰው የሚሉም አሉ በትውፊት። በዓላቸውም በላቲኑ ስርዓተ አምልኮ በዛሬው እለት በሊጡርጊያ የሚታሰብ ነው።እናት እና አባት ያለው መልአክ ወይ ከሰማይ የመጣ የለም ኢየሱስም ቢሆን ከእርሷ ስለተወለደ ነው ሰው የተባለው ስለዚህ ይሕ ክስ ልክ አይደለም።
5 ከመጽሐፍ ቅዱስ ጀምሮ ኢየሱስ ሰው መሆኑን የሚያስረዱ ጥቅሶች እንዲሁም የቤተክርስቲያን አባቶች እንደ ኢራንዮስ ኤፍሬም ዮሐንስ አፈወርቅ ዮስጢኖስ ሰማዕቱ ድንግል ማርያምን አዲሲቷ ሔዋን የሔዋን ተሀድሶ ብለው ማለታቸው ከክሱ በተቃራኒው የተከበረ እና የሚጠበቅ ትውፊት ነው። ከአባቶች ደግሞ በልዩነት ጎርጎርዮስ ዘኒሳ ጀርማኑስ ዘቁስጥንጥንያ ፉልበርት ዘቻርተርስ ወዘተ እናትና አባቷን በስም በመጥቀስ የጻፉ አባቶች ናቸው እንዲሁም ነገረ ክርስቶስንና ነገረ ማርያምን የዳሰሱ እንዲሁም የጉባኤያት ውሳኔ እና የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አስተምሕሮ የሆኑ ጽሁፎች እስከ ዘመናችን ድረስ አሉ። በተለይም ከ13ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በዚህ በዓል ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቶቻችንን ጨምሮ በየደብሩ የተሰበኩ ማስረጃወች ጽሁፎችና መልዕክቶች አሉ በተለይም በጣልያን የዛሬው በዓል ትልቅ በአል ተደርጎ ይከበራል በጀርመን ጥንታዊ የመዓድን አውጪወች ባልደረባ ተደርጋ ስለምትወሰድ በትልቁ ቅድስት ሀና በዚሁ እለት ትከበራለች። (ከሳጥኑ ውጪ ከማዕድን አውጪነት ወደ ገበሬነት ከተለወጠ ቤተሰብ የተወለደው ሉተር የመነኮሰው ለቅድስት ሐና ከመብረቅ አደጋ ለመትረፍ ተስሎ እንደነበር ልብ ይሏል)።
6 በጣም የሚያስጠላው ከሳሾቻችን ማስረጃ ሲጠየቁ (ሁሉንም አይደለም) ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ራሷን በጊዜ እያሻሻለች ስለመጣች ማስረጃ ስላጠፋች ማስረጃ ማግኘት አይቻልም ይሉናል። አንተ አጊኝተኸው እኛ ሳናውቀው ከሚል ድፍረታቸውን ከሚመጥን ቀልድ በቀር ለዚህ መልስ ያስፈልገዋል ብዬ አላስብም። ማስረጃ እና የማረጋገጥ ግዴታ ሲጠየቅ እኮ ማቅረብ አለበት ጋፍኛ ሁለተኛ ክስ ከመክሰስ። ይቅርታ እኮ ያባት ነው አላውቅም ማለትስ ማንን ገድሏል ።
7 በሰለጠነ ዘመን ሰው ጥቂት ፈልጎ ብዙ በሚያገኝበት ዘመንም ያልቆመ ክስ መሆኑ አሳዛኝ ነው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞች እና አልፎም መምሕራን ዘንድ ልዩነት ሲባል የሚጠራ ቁጥር አንድ ሐሳብ መሆኑ በዘንድሮ አመት የታተመ መጽሐፍ እንኳን (የኢትዮጵያ የሐይማኖት ተቋማትን የመዝሙር አስተዋጽኦ የሚቃኝ መጽሐፍ) ሐሳቡን ይዞ መገኘቱ እስከዛሬ የቀጠለ ክስ መሆኑን ያሳያል ይሔ ደግሞ እንኳን ላለን ግንኙነት ለእነሱ ለራሱ ውሸት ልክ ባለመሆኑ ሊታረም እና ሊያስታውሉት ይገባል ። ድንግል ማርያም ሀይለ አርያማዊት ናት አንልም።
ከዚህ ስር ታዲያ የበለጠ ማወቅ ለሚፈልግ ማግኘት የሚቻልበትን ማስረጃወች አስቀምጣለሁ። ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና ለምኑልን
Catholic Encyclopedia Immaculate Conception /The Encyclopedia Press
CCC 491
Fulgens Corona/ Pope Pius XII
Ineffabilis Deus/ Pope Pius IX
General Audience of 12 June 1996/ Pope John Paul II
Catholic Encyclopedia St. Joachim/ The Encyclopedia Press
The Gospel of the Nativity of Mary Chapter1/ Unknown author
Pius IX, "Ineffabilis Deus", December 8, 1854.
CCC 487
To the 3rd Public Session of the Pontifical Academies (November 7, 1998) 3/ Pope John Paul II
Encyclopedic Dictionary of the Christian East Theotokology / Edward G. Farrugia
Catholic Encyclopedia St. Joachim / The Encyclopedia Press
Catholic Encyclopedia St. Anne / The Encyclopedia Press
Catholic Encyclopedia The Blessed Virgin Mary / The Encyclopedia Press
Catholic Encyclopedia Apocrypha / The Encyclopedia Press
The Gospel of the Nativity of Mary Chapter 1 / Unknown author
An Exposition of the Orthodox Faith Chapter 14 / John of Damascus
Contra Faustum Book 23. 9 / Augustine of Hippo
Catholic Encyclopedia Immaculate Conception / The Encyclopedia Press
ምንጭ: ዲያቆን ራዕይ ሳሙኤል Facebook page የተወሰደ