በ2020 ከኖህ ሪልስቴት በተፈራረምነው የሽያጭ ውል የገዛናቸውን ቤቶች በ36 ወራት ሊያስረክቡን ተወስኖ… — Ethiopian Construction Vacancy & Tender — TG.ME

"በ2020 ከኖህ ሪልስቴት በተፈራረምነው የሽያጭ ውል የገዛናቸውን ቤቶች በ36 ወራት ሊያስረክቡን ተወስኖ ነበር። የውል ጊዜው ካለፈ ከ3 ዓመታት በላይ ቢሆንም ቤቶቻችንን አልተረከብንም " - ገዢዎች

ድርጅቱ ለደንበኞቹ ቤት በወቅቱ አለማስረከቡን አምኖ፣ ከመስረም 18 ቀን 2019 ዓ/ም ጀምሮ እንደሚያረክብ ቃል ገብቷል።

በአዲስ አበባ ወሰን አካባቢ በሚገኝ "Noah Hills" በተሰኘ የኖህ ሪልስቴት ፕሮጀክት አፓርታማ ገዢዎች ድርጅቱ በውሉ መሰረት ቤት እንዳላስረከባቸውና በቂ ምላሽ እንዳላገኙ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ አቤቱታቸውን ልከዋል። በተጨማሪም ቅሬታቸውን በስልክ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

አንዷ ገዢ በሰጡን ቃል፣ "የተፈራረምነው ቤቱን በሦስት አመታት ውስጥ ሊያስረክበን ነበር። አሁን ከውላችን ውጭ ስድስት አመት ሊሆን ነው ከተፈራረምን" ብለው፣ ምላሽ ሲጠይቁ አጥጋቢ መልስ እንዳልተሰጣቸው ይናገራሉ።

"እንዲያስረክቡን ለመጠየቅ ስንሄድ በጥበቃ ነው የሚያስወጡን፤ ወይም 'የሚመለከተው አካል የለም ውጭ ሀገር ነው' ይሉናል" ያሉት ቅሬታ አቅራቢዋ፣ ከሦስት ወር በፊት አንድ የድርጅቱን አካል አግኝተው እንደነበርና "15 ቀናት ስጡኝ" እንዳሏቸው፣ ሆኖም እስካሁን መፍትሄ እንደሌለ አስረድተዋል።

"ሥራው አልቋል፤ ለምን እንደማያስረክቡን አላወቅንም" ብለዋል። አፓርታማ ገዢዎቹ በውላቸው መሰረት ክፍያ ስለመፈጸማቸው ስንጠይቃቸውም፣ ለመጠየቅ ወደ ድርጅቱ የሚመላለሱት ሙሉ ክፍያ እንዳጠናቀቁ፣ ወደ 360 ከሚሆኑ ሰዎች አብዛኛዎቹ የቀራቸው በርክክብ ወቅት የሚከፈል 10% መሆኑን ተናግረዋል።

ሌላኛው ቤት ገዢ፣ "ሙሉ ክፍያ ከፍለን አቆዩት መስጠት አይፈልጉም። ሁለት ጊዜ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ አስገብተናል" ብለው፣ ለአንዱ ምላሽ እንዳልተሰጣቸው ገልጸዋል። ለማስረከብ "የማዘግየት፣ ጊዜ የመግዛት አይነት ጨዋታ ነው እየተጫዎቱ ያሉት" ሲሉ ወቅሰዋል።

"ወይ ከቤቴ አልሆንኩ፣ ወይ ከገንዘቤ አልሆንኩ" የሚሉት እኚሁ አካል፣ አስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። 

የተማረሩት ገዢዎቹ በዝርዝር ምን አሉ ?

" እኛ በ'Noah Hills' ፕሮጀክት ውስጥ አፓርታማ ገዢዎች፥ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2020 ጀምሮ ከኖህ ሪል ስቴት ጋር በተፈራረምነው የሽያጭ ውል መሠረት፣ የገዛናቸው የአፓርትመት ቤቶች በ36 ወራት ውስጥ እንደሚያስረከቡን በግልጽ ተወስኖ ነበር። ሆኖም የዚህ የውል ጊዜ ካለፈ ከሦስት ዓመታት በላይ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ቤቶቻችንን አልተረከብንም።

በተለያዩ ጊዜያት ለድርጅቱ በፅሑፍ ጥያቄዎችን አቅርበናል፤ ነገር ግን እስካሁን በቂ፣ ግልጽና የሚያሳምን ምላሽ አላገኘንም። ይህ ሁኔታ በገዢዎችና በድርጅቱ ላይ የነበረውን እምነት በእጅጉ አዳክሟል።

ለብዙ እንግልትና እምነት ማጣት ኪሳራ ውስጥ እንድንገባ ምክንያት ሆኗል።

ኖህ ሪል ስቴት የሚያቀርባቸው የመዘግየት ምክንያቶች ከሌሎች በተመሳሳይ ዘርፍ የሚሰሩ ድርጅቶች አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸሩ አሳማኝ ሆነው አልታዩንም። በተጨማሪም ድርጅቱ ቀድሞ የጀመራቸውን ፕሮጀክቶች ሳያጠናቅቅ ወደ አዳዲስ ፕሮጀክቶች መስፋፋቱ በብዙ ገዢዎች ዘንድ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል።

ይህም ከአዳዲስ ቤት ገዢዎች ገንዘብ መሰብሰብ ላይ ያነጣጠረ እንጂ ሙሉ ገንዘባቸውን ከፍለው ላለፉት 6 ዓመታት ቤታቸውን በመጠባበቅ ላይ ላሉ ደምበኞቹ ብዙም ግድ የማይሰጠውና ቃል የገባውን የውል ግዴታ የጣሰ መሆኑን ተገንዝበናል።

የፕሮጀክታችን ሁኔታ በግልጽ እንዲታወቅ እንፈልጋለን።

እንዲሁም አባላቶቻችን በግንባታ ቦታው ባደረጉት ጉብኝት አንዳንድ የግንባታ ጥራት ላይ የሚያስጨንቁ ጉዳዮችን ተመልክተዋል። እነዚህ ጉዳዮች በባለሙያና በተገቢ አካላት እንዲመረመሩ እንጠይቃለን።

ከዚህ በላይ የሚያሳስበን ጉዳይ ፦

የቤቶቹ መዘግየት በ100ዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች ላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ፣ የስነ-ልቦና እና የማህበራዊ ጫና ማሳደሩ ነው። ብዙዎቻችን የቤት ኪራይ እየከፈልን በተመሳሳይ የቤት ክፍያ በመክፈል በከባድ የገንዘብ ጫና እና የኑሮ መታወክ ውስጥ እንገኛለን።

ስለዚህ የምንጠይቀው፦

- ኖህ ሪልስቴት ለእያንዳንዱ ብሎክ ያለውን የግንባታ ሁኔታ፣ የቀሩ ስራዎችን እና ትክክለኛ የማስረከቢያ ጊዜ በግልጽ እንዲያሳውቅ፣

- ለዘገየው ፕሮጀክት ግልጽ ተጠያቂነት እንዲወስድ፣

- የሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት እና ተቆጣጣሪ አካላት ጉዳዩን በአፋጣኝ እንዲመረምሩት ነው።

ይህ መግለጫ የተዘጋጀው ማንኛውንም አካል ለማጥላላት ሳይሆን የገዢዎች ድምጽ እንዲሰማ፣ ግልጽነት እንዲኖር እና በህግና በውይይት መንገድ ፈጣን መፍትሄ እንዲገኝ በማሰብ ነው" ብለዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ የገዢዎቹን ቅሬታ ይዞ ኖህ ራልስቴትን ያነጋገረ ሲሆን፣ ድርጅቱም ለደንበኞቹ ቤት በወቅቱ አለማስረከቡን አምኖ፣ ከመስረም 18 ቀን 2019 ዓ/ም ጀምሮ እንደሚያረክብ ቃል ገብቷል

(የኖህ ሪልስቴት ሙሉ ምላሽ በቀጣይ ይቀርባል)

Via ቲክቫህ ኢትዮጵያ

@etconp
❤1👍1
September 9, 2026 884