ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ለተማሪዎች ሲሰጥ የቆየው የSTEM የክረምት ስልጠና ተጠናቀቀ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ STEM… — Dire-Dawa University — TG.ME

ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ለተማሪዎች ሲሰጥ የቆየው የSTEM የክረምት ስልጠና ተጠናቀቀ

በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ STEM ማዕከል ከአስተዳደሩ ከሚገኙ 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለተውጣጡ ተማሪዎች ለአንድ ወር ያህል ሲሰጥ የቆየው የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንጂነሪንግ እና ሒሳብ (STEM) ትምህርቶች የክረምት ስልጠና የዩኒቨርሲቲው አመራሮችና መምህራን በተገኙበት በይፋ ተጠናቋል።

በመዝጊያ መርሃ-ግብሩ ላይ ሰልጣኝ ተማሪዎች በስልጠና ቆይታቸው ባገኟቸው እውቀትና ክህሎት በመጠቀም ያዘጋጁትን የተለያዩ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ለታዳሚው አቅርበዋል። ከቀረቡት ፕሮጀክቶች መካከል፦
የግብርና መረጃ ሰጪ ድህረ-ገፅ፤
የምልክት ቋንቋን ወደ ፅሑፍና ድምፅ የሚቀይር አፕሊኬሽን (ጅምር ፕሮጀክት)፤
የትራፊክ እንቅስቃሴን የሚቆጣጠር የቴክኖሎጂ ስርዓት፤ እና
የተለያዩ የሮቦቲክስ ፈጠራዎች ተጠቃሽ ናቸው።

በስልጠናው ማጠቃለያ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር ተማም አወል ባስተላለፉት መልዕክት፣ የስልጠናው ዋና ዓላማ ተማሪዎች ለሳይንስና ሒሳብ ትምህርቶች ፍቅር እንዲያደርባቸውና ወደፊት ችግር ፈቺ የቴክኖሎጂ ባለቤቶች በመሆን ለሀገራቸው እድገት አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ማስቻል መሆኑን ገልጸዋል። ዶ/ር ተማም አክለውም፣ ስልጠናው ተማሪዎች ንድፈ-ሃሳብን ከተግባር ጋር አቀናጅተው የራሳቸውን ፈጠራ እንዲያበለፅጉ መሆኑን ጠቁመው፣ ዩኒቨርሲቲው ለፕሮግራሙ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የስልጠናው ተካፋይ የሆኑ ተማሪዎች በበኩላቸው፣ ለአንድ ወር የቆየው ተግባር ተኮር ስልጠና ለሳይንስ ትምህርት ያላቸውን እይታ እንደቀየረውና ወደፊት በሚመርጡት የሙያ መስክ ላይ ዝንባሌያቸውን እንዲለዩ ትልቅ አቅም እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።
❤20
September 5, 2026 3.3K 4