በሕይወቴ ከፈጸምኳቸው ትልልቅ ስህተቶች አንዱ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ከራሴ ግላዊ ፍላጎትና አስተሳሰብ ጋር በግድ ለማስማማት መሞከሬ፣ እንዲሁም በእግዚአብሔር ፈቃድ ምትክ በገዛ ድፍረቴ ባደራጀኋቸው አስተሳሰቦች መመራቴ ነበር። ይህ መንገድ መንፈሳዊ አደጋ ያለውና ለረጅም ጊዜ ውስጣዊ ሰላም አጣጥቼ እንድኖር ያደረገኝ ነበረ። ነገር ግን በዕድሜም ሆነ በመንፈሳዊ ሕይወት እያደግሁ ስመጣ፣ እውነተኛ ዕድገት ማለት እኛ ራሳችን ወደ እግዚአብሔር ቃል እውነት መጠጋትና መለወጥ እንጂ ቃሉን ወደ ራሳችን ሐሳብ ማውረድ እንዳልሆነ ተረዳሁ።
ይህን የእግዚአብሔር ቃል የበላይነትና እውነት አምኖ መቀበል ለልቤ ትልቅ ዕረፍትን፣ ለነፍሴም ምሉዕ ሰላምና ደስታን አምጥቶላታል። ይበልጥ እግዚአብሔርን እንድወደውና በቃሉ እንድደሰት ስላደረገኝ፣ ትእዛዛቱን መፈጸም በጸጋው የተነሣ ከባድና ሸክም ከመሆን ይልቅ የፍቅር መግለጫ ሆነልኝ። በእርግጥም እግዚአብሔርን መውደድ ማለት ሕጉን መውደድና በፈቃዱ መመላለስ መሆኑን ተረድቻለሁ።
@Christisallsufficient







