አዲስ ሪፖርተር - NEWS: post #30868 — TG.ME

የ8 ሰዓት የእንቅልፍ ህግ ጊዜው አልፎበታል ተባለ፡ አንድ ሰው በእርግጥ ምን ያህል ሰዓት መተኛት አለበት?

​ለዘመናት ሰዎች በቀን ውስጥ ስምንት ሰዓት መተኛት አለባቸው የሚለው እምነት የተሳሳተና ጊዜው ያለፈበት መሆኑን አዳዲስ የህክምና እና የሳይንስ ጥናቶች ይፋ አደረጉ።

​በቅርቡ በ”ብሬን ሜዲሲን” ሳይንሳዊ መጽሔት ላይ የወጡ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት፣ እያንዳንዱ ሰው እንደ እድሜው፣ እንደ ፆታው እና እንደ አካላዊ ሁኔታው የሚያስፈልገው የእንቅልፍ መጠን ይለያያል። የሰርይ ዩኒቨርሲቲ የፋክስ እና የእንቅልፍ ተመራማሪዎች እንዳረጋገጡት፣ የ8 ሰዓት የእንቅልፍ ህግ አመጣጥ በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ “8 ሰዓት ለስራ፣ 8 ሰዓት ለመዝናናት፣ 8 ሰዓት ለእንቅልፍ” በሚል ከተቀረጸ ማህበራዊ ፍልስፍና እንጂ ፍጹም ሳይንሳዊ መሰረት ያለው አይደለም።

​ተመራማሪዎች የኤሌክትሪክ መብራት እና የቴክኖሎጂ ውጤቶች በሌሉባቸው ጥንታዊ የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ ባደረጉት ጥናት፣ ሰዎች በቀን ከ5.7 እስከ 7.1 ሰዓታት (በአማካይ 6.4 ሰዓት) ብቻ ተኝተው ሙሉ ጤንነታቸውን ጠብቀው መኖር እንደሚችሉ አረጋግጠዋል። በተጨማሪም በዘመናዊው አለም ሰፊ የሰውነት እና የአእምሮ ምርመራ ያደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ ለሰው ልጅ አካላዊ ጤንነት እና ለአካል ክፍሎች እድሜ ማደስ አነስተኛ እና ተስማሚ የሚባለው የእንቅልፍ መጠን ከ6.4 እስከ 7.8 ሰዓታት መካከል ነው።

​የአሜሪካ የብሔራዊ የእንቅልፍ ፋውንዴሽን መረጃ እንደሚያመላክተው፣ እድሜያቸው ከ26 እስከ 64 ባሉ አዋቂዎች ዘንድ ከ7 እስከ 9 ሰዓት መተኛት የተለመደ ቢሆንም፣ ለአንዳንዶች ግን ከ6 እስከ 10 ሰዓት ባለው ውስጥ መተኛት ተፈጥሮአዊ ሊሆን ይችላል። ከተፈለገው መጠን በላይ አብዝቶ መተኛትም ሆነ አነስተኛ እንቅልፍ ማግኘት ለልብ ህመም፣ ለስትሮክ እና ለክብደት መጨመር እንደሚያጋልጥ በጥናቱ ተመልክቷል።

@Addis_Reporter
@Addis_Reporter
❤21👍3🤔2🤪2
August 27, 2026 3.8K 14