#የተማሪዎችድምጽ 📢
የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ (ASTU) ተማሪዎች "ካፌ ለማይጠቀሙ" (Non-cafe) ተማሪዎች የሚከፈለው የምግብ ክፍያ እና የወጪ መጋራት (Cost-sharing) ስሌት ላይ ከፍተኛ የአሰራር ግድፈትና የፋይናንስ ችግር እንዳለ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በፅሁፍ ቅሬታ አስገብተዋል።
ተማሪዎቹ እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ያልተቀበሉትን ገንዘብ እንደ ዕዳ በመመዝገብ ለከፍተኛ የገንዘብ ጫና እየዳረጋቸው ይገኛል።
ተማሪዎቹ ጉዳዩን በዝርዝር ለማስረዳት የሚከተሉትን ነጥቦች አቅርበዋል።
1. በአንደኛ ሴሚስተር በፖርታል ላይ የተመዘገበው የወጪ መጋራት ዕዳ 15,000 ብር ነው። ሆኖም ተማሪዎች ከመስከረም እስከ ጥር ድረስ በድምሩ የተቀበሉት 12,800 ብር ብቻ ነው። በዚህም 2,200 ብር ሳይቀበሉ ዕዳ ተደርጎባቸዋል።
2. በሁለተኛው ሴሚስተር ፥ አሁንም በፖርታል ላይ 15,000 ብር ዕዳ ተመዝግቧል። ተማሪዎች እስካሁን (ከየካቲት እስከ ሚያዚያ) የተቀበሉት 9,000 ብር ብቻ ነው።
ተማሪዎች አሁን የሚገኙት በግንቦት ወር ሲሆን፣ ዩኒቨርሲቲው የተለመደውን የ3,000 ብር ክፍያ ብቻ ልኮ ዝም የሚል ከሆነ በቀሪው ክፍያ ላይ ከፍተኛ ክፍተት ይፈጠራል። ተማሪዎቹ " በግንቦት ወር ዕዳው እንዲካካስልን 6,000 ብር ሊላክልን ይገባል " ይላሉ።
አሁን ባለው አካሄድ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ ተማሪው እጁ ላይ ሳይደርስ በእዳ እንደሚያዝ ጠቁሙዋል። እጃቸው ላይ ሊደርስ የሚገባው ገንዘብ የት እንደሚደርስ ምንም እውቅና እንደሌላቸው አስረድተዋል።
" ያልተጠቀምንበትን አንከፍልም " - ተማሪዎች
ተማሪዎቹ እንደሚሉት፤ አንድ ተማሪ በዓመት ውስጥ በአማካይ ከ3,000 እስከ 6,000 ብር ያልተጠቀመበትን እና በእጁ ያልገባን ገንዘብ እንደ ዕዳ እንዲከፍል ይገደዳል። " ይህ ከፍተኛ የፋይናንስ ጉድለት እና የአሰራር ብልሹነት ነው " ብለዋል።
" ብዙ የድሃ ልጆች ባለንበት ሁኔታ ያልተጠቀምንበትን የመክፈል ግዴታ የለብንም " ሲሉ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።
ይህንን ከፍተኛ የፋይናንስ ስሌት መዛባት በተመለከተ ለሚመለከተው የዩኒቨርሲቲው የስራ ሃላፊዎች ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ እስካሁን መፍትሄ ለመስጠት ፍቃደኛ የሆነ አካል አለመኖሩን ተማሪዎቹ ጠቁመዋል።
ተማሪዎቹ፦
- ትምህርት ሚኒስቴር እና የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር በወጪ መጋራት ስሌቱ ላይ አስቸኳይ ግምገማ እንዲያደርጉ።
- በተማሪዎች ስም የሚመዘገበው ዕዳ ተማሪዎች በእጃቸው ከሚረከቡት ገንዘብ ጋር እኩል እንዲሆን።
- ተማሪዎች ካልተጠቀሙበት የዕዳ ጫና ነጻ ሆነው ትምህርታቸውን እንዲያጠናቅቁ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ... ጥሪ አቅርበዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ የተማሪዎቹን ቅሬታ ይዞ ተቋሙን ለማነጋገር ጥረት ቢያደርግም ለጊዜው አልተሳካም። ማብራሪያ እንደደረሰን ወይም ከዩኒቨርሲቲው አስተዳደር በኩል የሚሰጠውን ምላሽ ተከታትሎ የሚያቀርብ ይሆናል።
ቲክቫህ
ለጥቆማ 👉 @atc_newsbot
➡️ https://t.me/atc_news