ሰበር''ኢሰመጉ በምስራቅ አርሲ ከ450 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ይፋ አደረገ''
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) በኦሮሚያ ክልል፣ ምስራቅ አርሲ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች ''ከ2014 ዓ.ም እስከ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ'' በተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ያካሄደውን የምርመራ ግኝት ይፋ ባደረገበት 158ኛ ልዩ መግለጫው፣ ቢያንስ ከ450 በላይ ንጹሃን ዜጎች መገደላቸውን አስታወቀ።
ሀገር በቀሉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟገች ድርጅት በ37 ገጾች ቀንብቦ ባወጣው ሪፖርት መሠረት፣ በዞኑ በሚገኙ ዘጠኝ ወረዳዎች ውስጥ በታጣቂ አካላት ማንነትንና ኃይማኖትን መሰረት በማድረግ በተፈጸሙ ጥቃቶች የሰው ህይወት ከማልፉ ባሻገር፣ በርካታ ዜጎች ለአካላዊ ጉዳት፣ ለእገታ እና ለአስገድዶ መሰወር ተዳርገዋል።
በተጨማሪም ከ14,000 በላይ ሰዎች ከቀያቸው የተፈናቀሉ ሲሆን፣ በርካታ አብያተ ክርስቲያናትና የግል ንብረቶች መዘረፋቸውንና መውደማቸውን አመልክቷል።
ኢሰመጉ ባካሄደው የመስክ ምልከታና መረጃ የማሰባሰብ ስራ፣ በጥቃቶቹ ሳቢያ በየወረዳው የተመዘገበውን የሟቾች ቁጥር እንደሚከተለው አሰናድቶታል፡፡
መርቲ ወረዳ፣ 117 ሰዎች፤ ሽርካ ወረዳ፣ 116 ሰዎች፤ ጀጁ ወረዳ፣ 101 ሰዎች ፤ ሮቤ ወረዳ፡ 47 ሰዎች ፤ ጉና ወረዳ፣ 26 ሰዎች ፤ ሆንቆሎ ዋቤ ወረዳ፣ 20 ሰዎች ፤ ሙኒሳ ወረዳ፣ 19 ሰዎች ፤ አሰኮ ወረዳ፡ 5 ንጹሃን ዜጎች እና 4 የህዝብ ሚሊሻዎች ፤ አርሲ ሲሬ ወረዳ፣ 3 ሰዎች በተጠቀሰው የጊዜ ሰሌዳ ውስጥ ሕይወታቸው አልፏል፡፡
ጉባኤው የሟቾችን ስም ዝርዝር ከነምስላቸው አስደግፎም ነው በሪፖርቱ ይፋ ያደረገው፡፡
ከግድያው ጎን ለጎን በሽርካ፣ ሮቤ፣ ጀጁ፣ መርቲ እና ሙኒሳ ወረዳዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በታጣቂዎች ታግተው የተወሰዱ ሲሆን፣ ቤተሰቦቻቸው ከፍተኛ የካሳ ገንዘብ ከፈለው ያስለቀቋቸው ቢኖሩም፤ የበርካቶች ያሉበት ሁኔታ እስካሁን ሳይታወቅ ቀርቷል። በጥቃቶቹ ወቅት በህጻናትና በአረጋውያን ላይ ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱንም ሪፖርቱ ያመላክታል።
የደህንነት ስጋቱ በዞኑ ከፍተኛ መሆኑን የጠቀሰው መግለጫው፣ በጀጁ (6,216)፣ በሽርካ (3,746)፣ በአሰኮ (2,133)፣ በሮቤ (1,270)፣ በመርቲ (1,036)፣ በሙኒሳ (29) እና በጉና (21) ወረዳዎች በጠቅላላው ከ14 ሺህ በላይ ዜጎች መፈናቀላቸውን አስረድቷል። በተጨማሪም ዕድሜ ጠገብ አብያተ ክርስቲያናት መቃጠላቸውን፣ መዘረፋቸውንና በስጋት ምክንያት መዘጋታቸውን ይፋ አድርጓል።
ኢሰመጉ ድርጊቶቹ በህገ-መንግስቱና በዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች የተረጋገጡ መሰረታዊ መብቶችን የጣሱና በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ባህሪያትን የሚያሳይ ነው ብሏል።
በመሆኑም የፌደራልና የክልል መንግስታት ለዜጎች ዘላቂ ጥበቃ እንዲያደርጉ፣ ጥሰት ፈጻሚዎችን ለፍርድ እንዲያቀርቡ፣ ለተጎጂዎች ካሳ እንዲከፈልና ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ጥሪ አቅርቧል።
ዘገባው የአዲስ ማለዳ ነው