ወደ ባህል ሀኪም ሪፈር ፅፌ አውቃለሁ
========================
ጠቅላላ ሀኪም እያለሁ ቤኒሻንጉል ክልል የህንድ ድርጅት ውስጥ እሰራ ነበር። አካባቢው ላይ ብዙ ተሳቢና ተራማጅ እንስሳት ነበሩ። ከእነዚህ መካከል አንዱ ጊንጥ ነው። ህክምና ት/ቤት እያለሁ ጊንጥ የነደፈውን ሰው እንዴት እንደሚታከም የተማርን አይመስለኝም።
የጊንጥ ንድፊያ (Scorpion sting) እጅግ በጣም ያማል። የንብ ወይም የተርብ ንድፊያ ከጊንጥ ጋር ሲወዳደር እንደመዳሰስ ነው። የህንዶቹ ሀላፊ ጊንጥ ነድፎት እነጮኸ መጣ። Up to date መፅሀፍ ከፍቼ ህክምናውን አነበብኩ። አላርጂክ ሆኖበት ሰውነቱ ካበጠ ወይም የአየር ቱቦ ከተዘጋ ከባድ ነው። አለበለዚያ ግን የተነደፈበትን ቦታ በሳሙናና በውሀ አጥቦ ቀዝቃዛ ነገር እንዲያደርግበት መምከርና የህመም ማስታገሻ መስጠት ነው።
ማስታገሻ ብሰጠውም ህመሙ አልቀነሰለትም። በአካባቢው የባህል ሀኪም እንዳሉ ሰማን። ህንዱ "መሄድ እፈልጋለሁ" አለ። ተስማምቼ ወደ ባህል ሀኪሟ መሄድ እንደሚችል ነገርኩት። ህክምናውን ለማየት እኔም አብሬው መኪናው ላይ ወጣሁ።
የባህል ሀኪሟ ጋር ስንሄድ እንደመፋቂያ ያለ እንጨት ጉድጓድ ነገር ውስጥ እያሽከረከሩ ሲግል ጊንጥ የነደፈው ዙሪያ ሰውነቱን ተኮሱት። ስንመለስ ህንዱ "ትንሽ ቀንሶልኛል" አለ። የተካሄደው ህክምና ሌላ ህመም በመፍጠር ከዋነኛው ህመም የማዘናጋት (Distraction therapy for pain) ይሁን አይሁን አላውቅም።
ወደ ክሊኒኩ ተመልሰን ስንገባ ህንዶቹ ተሰብስበዋል። እዛ የሚሰሩት ህንዶች አለቃ በጣም ነው የሚፈሩት። አለቃቸውን ለማፅናናት የተለያየ ነገር መናገር ጀመሩ።
ወታደር ቤት ውስጥ የ'ሰር ሳንድዊች' የሚባል አነጋገር አለ። መጀመሪያ እና መጨረሻ ላይ 'ሰር' ማለት ነው። ለምሳሌ 'ሰር የስ ሰር' (Sir, yes sir) እዛ የነበሩት ህንዶች ግን አለቃቸውን ስለሚፈሩት ሲናገሩ የሰር ፍርፍር ነበር። አንዱ እየተርበተበተ አለቃውን ለማፅናናት "ሰር ሱኒል ሰር ዶንት ዎሪ ሰር። ስኮርፒዮን ሰር ኢዝ ፔንፉል ፈርስት ታይም ሰር። በት ኔክት ታይም ሰር ኢት ዊል ቢ ሌስ ፔንፉል ሰር" አለ።
ሚስተር ሱኒል በንዴት ጥርሱን ነክሶ አፍጦበት "ጭራሽ ኔክስት ታይም ትመኝልኛለህ?" አለው።
20
6
1
1April 14, 2026 4.2K 2 3