ስለ እናንተ አመሰግናለሁ! ግንቦት 1, 2017 ዓ/ም ምሽት ነበር። ቀዶ ጥገናው ተጠናቅቆ በተሽከርካሪ አልጋ… — yero's reflections/ የየሮ ንጽረቶች — TG.ME

ስለ እናንተ አመሰግናለሁ! ግንቦት 1, 2017 ዓ/ም ምሽት ነበር። ቀዶ ጥገናው ተጠናቅቆ በተሽከርካሪ አልጋ እየተገፋው ወደ ኮሊደሩ አደረሱኝ፤ አልጋውን እየገፋ ከነበሩት የህክምና ባለሙያዎች ውስጥ አንዷ ከኮሊደሩ መግቢያ ላይ ተሰብስቦ የሚጠብቀኝን የሰው ብዛት ተመልክታ "ማህበራዊ ሕይወትህ ጥሩ ነው ማለት ነው፤ ብዙ ሰው ነው እየጠበቀህ ያለው።" አለችኝ። እውነቷን ነበር ከምሽቱ 3:00 ገደማ የደህንነቴ ጉዳይ ግድ ብሏቸው ቀዶ ጥገናው አልቆ እስክወጣ የሚጠብቁኝ ብዙ ወዳጆች..... ያ ወቅት ሰዎች ለእኔ ያላቸውን ፍቅር በጥልቀት እንዳስተውል ካደረጉኝ ወቅቶች ውስጥ አንዱ ነበር። ከህክምና ባለሙያዎች ይጀምራል፤ በህክምና ወቅት ከምርመራ አንስቶ በቀዶ ጥገናውና ከዚያ በኋላ በነበረኝ የክትትል ቆይታ ያሳዩኝና የሰጡኝ እንክብካቤ ግሩም ነበር። ወደ ሙሉ ጤንነቴ እስክመለስ ድረስ በዕየለቱ እመለከተው የነበረውን ፍቅር ያስደንቀኝ ነበር። ለቀዶ ጥገና ወደ ሆስፒታል 'ሪፈር' መደረጌን ሰምተው ከእኔ አስቀድመው በሆስፒታል የተገኙ ጓደኞች ነበሩ። ድካምና ህመም ተጫጭኖኝ እንቅልፍ ቢታገለኝም በላይ በላይ የሚጎበኝ ሰው ከመምጣት ስለማያቋርጥ ከእንቅልፍ እየታገልኩ ያሳለፍኩባቸው ቀናቶች ነበሩ። ሌላ ግዜ ደግሞ እንቅልፍ አሸንፎ ሲጥለኝ አጠገቤ የነበሩ ወዳጆቼ ከሰዓታት በኋላ ስነቃ ያንን ሁሉ ሰዓት ሳይሰላቹ ሲጠብቁኝ አገኛቸዋለሁ። የቤተሰብ ፍቅር፣ የጓደኞች ጥልቅ ወዳጅነት፣ የስራ ባልደረቦቼ የጠነከረ አብሮነት፣ የቅዱሳን ያልተገደበ መሰጠት፣ የሰፈርና የጎረቤት ቀድሞ ደራሽነትን መመልከት የቻልኩበት ነበር። ጭምትና ቁጥብ እንደሆንኩ የሚሰማኝ እኔ በሰዎች ተከብቤ ራሴን ሳገኝ እደነቅ ነበረ። በአካል መገኘት ያልቻሉ ስልክ ለመመለስ እስከሚደክመኝ ድረስ እየደወሉ ጠይቀውኛል። አይኔን በአይናቸው ያላዩ ሩቅ ያሉት የLAD ወገኖቼ ደጋግመው ይደውሉልኝ ነበር። ለእኔ ያላቸው እይታ አሉታዊ እንደሆነ የማስባቸው ሰዎች ሳይቀሩ በዚህ ወቅት አጠገቤ ከመሆን አልቦዘኑም። ዛሬ ላይ በወቅቱ ስላሳለፍኩት አስቸጋሪ ነገር አሊያም ህመም ይህ ነው የሚባል ትውስታ የለኝም። ቆጥሬ የማልጨርሳቸው የወዳጆቼን ፍቅር፣ ርህራሄ፣ ትኩረትና እንክብካቤ የአስቸጋሪውን ገጽታ ቦታ ጠቅልሎ ወስዶታል። ከእኔ በላይ ለእኔ የተጨነቁልኝ፣ ብዙ ነገራቸውን ትተው አጠገቤ የተገኙልኝ፤ ትኩረታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ፍቅራቸውን ከልብ ያሳዩኝ እልፍ ወዳጆች። ለሳምንታት በአልጋ ላይ ያሳለፍኩትን ጊዜ እንደምንም እንድቆጥረው ያደረጉኝ ቅን ልቦች። እግዚአብሔር ስለሰጠኝ ወዳጆች ባሰብኩ ቁጥር ከማመስገን በቀር ቃላት አጣለሁ። አዎን ስለ እናንተ አመሰግናለሁ!

September 13, 2025 486