እጠብቃታለሁ....ደግሞም ትመጣለች በውል የሚታወቅ ቀጠሮ ኑሮኝ አይደለም፤ እመጣለሁ ብላለችና ከቃሏ ዝንፍ እንደማትል ስለማውቅ እጠብቃታለሁ። "እመጣለሁ" ብላ ቃሏን ባትሰጠኝ እንኳን "ትቀር ይሆን?" የሚል ጥርጣሬ ለአፍታ አይገባኝም። ከዛሬ ነገ መጣች እያልኩ ደጅ ደጁን እያየሁ እጠብቃታለሁ። የውጩው በር "ጓ" ባለ ቁጥር ጫማ እንኳን ሳላጠልቅ፣ "ማን ነው?" ለማለት ትንፋሽ ሳላገኝ ተንደርድሬ በሩ ላይ ደርሼ እበረግደዋለሁ። በሩን እንደከፈትኩ እርሷ ቁማ የማገኛት ይመስለኛል፤ እንደ ሌላው ጊዜ። የናፈቀ ልብ ሁኖብኝ እንጂ የእርሷን ማንኳኳት የተለየ ነው። ስንታንኳኳ አታቋርጥም፤ በሩ እስኪከፈት ዝም ብሎ መቀጥቀጥ። "ድም ድም ድም...." "ማን ነው?" "ድም ድም ድም..." "ኧረ ማን ነው? እየመጣሁ ነው።" "ድም ድም ድም... በቃ እንዲህ ነች፤ የአጥሩን በር እስከፍትላት ሳታቋርጥ ታንኳኳለች። ለዛ ይመስለኛል ዘንድሮም በሩ ሲንኳኳ "ማን ነው?" ብዬ ሳልጠይቅ እየሮጥኩ ሄጄ በሩን የምከፍተው። እርግጥ የእኔና የእርሷ የፍቅር ታሪክም የሚጀምረው እዚሁ በር ላይ ነው። ይህንኑ በር ካለማቋረጥ ያንኳኳች ቀን፤ አስታውሳለሁ... "ድም ድም ድም..." "ማን ነው?" "ድም ድም ድም..." "ኧረ ማን ነው?" "ድም ድም ድም....." ማንኳኳቱ አይቋረጥም እየተበሳጨሁ ድርሼ በሩን ስከፍት፤ ቁጣዬን አብንንኖ የሚያጠፋ ውብት የተላበሰች እንስት ደጄ ላይ ተሰይማለች። ቁንጅና ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያስደነግጠኝ? ሺቲ ነገር ለብሳለች። ደርበብ ያለ ሰውነት አላት። የሚያማምሩት አይኖቿ ርህራሄ የተሞሉ ናቸው። ከፊቷ ላይ የሚነበበው ፈገግታ ካለምን የሰላምታ ቃል ሰላምን ያሰፍናል። ዬት ነበር የማውቃት? ከሰፈራችን ሁለተኛው ቅያስ ላይ ካለው ሱቅ ውስጥ ተቀምጣ በውልብታ እንዳየኋት ትዝ አለኝ። "አሁን ቡና ስትገዛ..." አለችኝ ሱቅን በእጇ እየጠቆመችኝ። "...ስኳር ረስተሃልና...መፈለግህ አይቀርም ብዬ ነው።" አለች በፌስታል የተቋጠረውን ስኳር ለማቃበል እየዘረጋች። ግራ ገባኝ፤ ልቀበላት አልቀበላት? እኔ ቡና በስኳር አልጠጣም ልበላት? ስኳሩን ለማቃበል እጇን እንደዘረጋች "በል ቶሎ ተቀበለኝ ቡና የምታፈላልህ እዚህ አይታኝ ዘራፍ እንዳትል" አለች ጠንጠራርታ ከእኔ አሻግራ ቤት ውስጥ ለመመልከት እየሞከረች። ፈገግ ብዬ "ኧረ ቡና የሚያፈላ የለም፤ ለራሴ ነው የማፈላው።" ከማለቴ ስኳር ያልያዘውን እጇን አፏ ላይ አድርጋ "ሂድ! ጀበና ጥደህ ምናምን?" አለች ሳቅ እያለች። "አይ በቦይለር ነው የማፈላው።" "ውይ ምስኪን፣ ቡና በቦይለር? እኔ ላፍላልህ?" ብላኝ እሺታዬን እንኳን ሳትጠብቅ አልፋኝ ወደ ግቢው ቀጥላ ወደ ቤት ገባች። እንዲህ እንደ ቀልድ ነበር ወደ ቤቴም ወደ ልቤም የገባችው። ሳታስፈቅደኝ፤ ሰተት ብላ። ይቀጥላል.....
እጠብቃታለሁ....ደግሞም ትመጣለች በውል የሚታወቅ ቀጠሮ ኑሮኝ አይደለም፤ እመጣለሁ ብላለችና ከቃሏ ዝንፍ… — yero's reflections/ የየሮ ንጽረቶች — TG.ME
August 3, 2025 338 2