የዩኒቨርስቲ ተማሪ እያለሁ ያየሁት ድራማ ነበር፤ "ፌውሎሺፕ" ውስጥ። አንድ እግዚአብሔር ነገ ቤትህ እመጣለሁ… — yero's reflections/ የየሮ ንጽረቶች — TG.ME

የዩኒቨርስቲ ተማሪ እያለሁ ያየሁት ድራማ ነበር፤ "ፌውሎሺፕ" ውስጥ። አንድ እግዚአብሔር ነገ ቤትህ እመጣለሁ ስላለውና ቀኑን ሙሉ እርሱን በመጠባበቅ የዋተተን ሰው ሕይወት የሚያስቃኝ። ሰውዬው የእግዜሩን መምጣት ተስፋ አድርጎ ቤቱን አሰናድቶ፣ ለከበረ እንግዳ የሚገባ አቀባባል ለማድረግ ይጠባበቃል።

በዚህ ጉጉት በተሞላበት ጥበቃ መሃል በሩ ይንኳኳል፤ "እንግዳዬ መጣ" ያለው ባለቤት ወደ ደጅ ይጣደፋል፤ ከደጅ ያገኘው ግን አንድ ጎስቆል ያለች ህጻን የተሸከመች ሴት ነበረች። ሴትዮዋ ህጻኑ ከነጋ ምግብ አለመቅመሱን አስረድታ ቁራሽ ለመነች። ሰውዬው "ባልጠፋ ቀን...." በሚል አኳሃን የከበረ እንግዳ እየተጠባበቀ መሆኑን አብራርቶ፤ ሌላ ቀን እንድትመለስ ነግሯት ሸኛት። ቀጥሎ ሌላ መንኳኳት....ሌላ እራፊ ጨርቅ የሚፈልግ ወጣት....ተመሳሳይ መልስ...በሩ ይዘጋል። ደግሞ ሌላ መንኳኳት ....የታመመና ማረፊያ ያጣ ህመምተኛ.....ተመሳሳይ መልስ...በሩ ይዘጋል።

ቀኑ እየመሸ ሄደ፤ ዕለቱን በሞላ ሲጠበቅ የነበረው እግዜር ግን ብቅ አልል አለ። ይህኔ ሰውዬ በምሬት ወደ ጸሎቱ ተመለሰና "እመጣለሁ ብለኸኝ ቀኑን ሙሉ አስጠብቀከኝ ቀረህ። ለምን?" እያለ መጠየቁን ገባ።
እግዜርም "መምጣትማ መጥቼ ነበር፤ ያውም ደጋግሜ"
ሰውዬ "ኧረ በጭራሽ፤ ቀኑን ሙሉ ነቅቼ ስጠብቅህ ውዬ"
እግዜሩ "መጥቼ ነበር ታርዤ አላለበስከኝም፤ መጥቼ ነበር ርቦኝ አላበላኸኝም፤ መጥቼ ነበር ታምሜ አላስታመምከኝም.....።" ለካስ እግዜሩ መጥቶ ነበር። ደጋግሞ!

አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ከእግዚአብሔር ጉብኝት እንዲሁ ይተላለፉሉ። አጥብቀው ለፈለጉትና ተግተው የናፈቁትን ጉዳይ ለመቀበል ሲጠባበቁ ቢውሉም ቅሉ፤ ፍላጎታቸውንና መሻታቸውን ይሞላ ዘንድ፤ ጸሎታቸው መልስ ይበጅለት ዘንድ ታምራዊ ጉብኝ ወደ ሕይወታቸው ሲመጣ መቀበል ተስኗቸው፤ የተንኳኳው ደጃቸውን መክፈት ለግመው ከመልካም በረከት እንደዘበት የሚጎድሉ ብዙሃን ናቸው።

በእርግጥ ይሄ መተላለፍ አንዳንዴ ባለማወቅ ሊሆን ይችላል፤ ሁኖም ሁሌም በአለማወቅ ሊሳበብ ግን አይገባም። አንዳንዴ በቸልተኝነት፣ ሌላ ጊዜ እብሪተኝነት፤ ምናልባት 'Ego' ፈርጥሞ፤ እኔ ያልኩት ካልሆነ የሚል ድርቅና ደርጅቶ....ብቻ በሌላም በሌላም ብዙ በቀጠሮቸው በአድራሻ ተገኝተው "ኖሩ" ያልተባሉ ባይተዋር በረከቶች አሉ።

ሁላችንም ልንረዳው ግድ የሚለን ቁምነገር፤ "ብዙዎች የምንፈልገውን ያጣነው ስላልተሰጠን ሳይሆን ስላልተቀበልን መሆኑን" ነው። በአንዳንድ ከሰነበተ የህይወት ትርምስ ጀርባ ከአምላክ ዝምታ ይልቅ ባለመታዘዝ የባከኑ ብዙ እድሎች፣ በቸልኝነት የተበላሹ  ብዙ አጋጣሚዎች ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ።

በእርግጥ ይሄ ምቾት የሚሰጥ ሃሳብ አይደለም፤ በትርምስ ለተሞላ ሕይወታችን ጣታችንን ወደማንም ላንቀስር ከራስ ጋር የሚያፋጥጥት ሃቅ ነው። ላለፍንባቸው ቀውሶች ሃላፊነት እንድንቀበል የሚሞግት አስፈሪ ድምጽ!  ግና ደግሞ እውነት ነው፤ ሸሽተን የማናመልጠው፤ ጨፍነን የማናሳልፈው።

እንግዲያውስ አቀበት ለሆኑብን አዙሪቶች መልስ ከፈለግን ቆም ብለን ያለፍንበትን መንገድ እናስተውል። አምላክን ከማማረር፤ በእድላችን ከማላዘን ወደ ራስ እንመልከት። ያን ጊዜ ማስተካከልና ማረም የምንችላቸውን ብዙ ነገሮችን ለማቃናት እድል እናገኛለን። ከዚያም በላይ ነገም መልካም ጉብኝቶች ደጋግመው መምጣታቸው አይቀርምና ሌላ መተላለፍ እንዳይፈጠር ጥንቁቅ እንሆናለን። ስለትናንት ሃላፊነት ሳንወስድ የተሻለ ነገን መጠበቅ አንችልምና!

ብዙ ነገር ያጣነው ስላልተሰጠን ሳይሆን ስላልተቀበልን መሆኑን እናስተውል ይሆን?

https://t.me/Yeroreflect
❤10🥰3👍2
July 17, 2025 323 5