ለትውስታ የጥበብ ቤት 13ኛ ዙር ላይ የቀረበ . ኢክራም ለምን አገባች? . (#ፈይሠል_አሚን) . ብታጥርም፣ረዣዥም ሰዎች ሁሉ እቤቷ እየመጡ ለትዳር ይጠይቋታል፡፡እንቢ ትላለች፡፡ከስታ እንደፓስታ ቀጥ ያለች ብትሆንም ደንደን ያሉ ወንዶች ላግባሽ እያሉ ቤቷ ይንጋጋሉ፡፡ የመንደሩ ወንዶች ሁሉ ለየብቻ ቢተኙም በጋራ ሕልም ያያሉ፤ኢክራምን አግብቶ በዝቶ ተባዝቶ መኖርን ያልማሉ፡፡እሷም አይሰለቻትም፤ የመጣውን ሁሉ ኢማን የለውም እያለች ታባርራለች፡፡ . በኢማን ምክንያት ብዙ ሰው ማባረሯን የሚሰማ ጠያቂ ሱሪውን በተካነ ሰፊ አሳጥሮ፤ጺሙን በባለሙያ አስበጥሮ ደረቱን ወጥሮ ይመጣል፡፡ ኢክራም እንዴት እንደምታውቅ ባላውቅም እንቢ ትለዋለች፡፡ለምን ሲሏት ኢማን የለውም ነው መልሷ፡፡ ሁሉም ሰው ኢማን አለው ብሎ የሚመሰከርለት የመስጊዱ ሙዓዚን ኢክራምን ለትዳር ከጠየቁ በርካታ ሰዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ኢክራም ግን ኢማን የለውም ብላ እንቢ ስትል አባቷ ራሱ ቱግ አሉ፡፡‹‹ከዚህ በላይ ሶሐባ ነው እንዴ የምትፈልጊው?›› አሏት፡፡ . ሰፈሩ ጉድ አለ፤‹‹ይህቺ ልጅ የኢማን ደረጃዋ መጥቋል››ተባለላት፡፡ሰዎች በመንገድ ሲያገኙዋት ጎንበስ ቀና እያሉ እየተቅለሰለሱ ሰላምታ ያቀርባሉ፡፡በቅርቡ አፍ የፈቱ ሕፃናት እንኳ በሚያምር ቅላጼያቸው ‹‹አሸላሙዓለይኩም!›› ይሏታል፡፡ ለእኩዮቿ አርዓያ ሆነች፡፡ኢክራም አደገች አሉ(በኢማን)፤ተመነደገች ተባለ፤ምክንያቱም ኢክራም ኢማን አላት! ወላጆች ልጆቻቸውን ‹‹እንደ ኢክራም ኢማን ይኑርሽ!›› እያሉ መምከር ጀመሩ፡፡ . ኢክራም ሐዲስ ነግራኝ ታውቃለች፡፡ከምወድላት ነገር አንዱ የተናገረችው ነገር የሰው አዕምሮ ውስጥ ዘልቆ መግባቱ ነው፡፡የተጠማ ውሻ ውኃ አጥታ ጀነት ስለገባችው ሴት ነገረችኝ፡፡እሷ ስትነግረኝ ልቤ ውስጥ ገባ! . እና ያን ሰሞን የተጠማ ውሻ ፍለጋ ስኳትን ሰነበትሁ፡፡ለምን እንደሆነ አላውቅም የተጠማ ውሻ አጠጥቼ ጀነት የምገባ የምገባ መሰለኝ፡፡ ችግሩ የተጠማ ውሻ ፈልጌ አጣሁ፡፡መጨረሻ ላይ በጠራራ ፀሐይ መንገድ ላይ የተጋደመ ውሻ አይቼ አብሮኝ ሲፈልግ በደከመ ማስታጠቢያ ውኃ አቀረብሁለት፡፡ውሻው ግን በአፍንጫው ሸተት አደረገና ቀና ብሎ ገላመጠኝ፡፡የባንቧ ውኃ ብሠጠውም ፣የታሸገ ውኃ ሳይሆን አይቀርም የፈለገው፡፡ኢክራም ‹‹ኢማን ያለው . . . ሰው አይገፋም!›› ያለችው ትውስ አለኝና. . .ይሄ ውሻ ኢማን የለውም ብዬ ደመደምኩ! . ያልተጠማና የቀበጠ ውሻ ውኃ አጠጥቼ ጀነት አልገባም ብዬም ኢክራም ጋር ሌላ ሐዲስ ልጠይቅ ሄድኩ፡፡ . ስሄድ ‹‹ኢክራም ልታገባ ነው›› የሚል ወሬ ሰማሁ፡፡አይገርምም? ኢክራም ልታገባ ነው! እንዳሰብሁት አልነበረም፡፡የኢክራም ባል ኢማን አለው፡፡ሦስት መኪናና ሁለት ድርጅትም አለው፡፡በዕድሜም ቢሆን ምራቁንም ገንዘቡንም ዋጥ ያደረገ ሰው ነው፡፡ . ኢማን አላት ብለን የደመደምንባትን ሴት ለመጀመሪያ ጊዜ በቬሎ አየኋት፤የተወጣጠረ ቬሎ፤ዓለም ላይ ለተጠሙ ውሾች ወንዝ መከራየት የሚችል ገንዘብ የፈሰሰበት ሠርግ ተሰረገላት፡፡ ቤተሰባዊ ሳይሆን ብሔራዊ ሠርግ ነበር የሚመስለው፤የመጣው ሰው ብዛት፣የቆመው የመኪና ዓይነት ልዩ ነበር፡፡በተለይ የምግብ ቡፌው እኔ በግሌ አይቼው አላውቅም፡፡ለምግብ መደርደሪያነት የተዘጋጀው ጠረጴዛ ረዥም ስለሆነ ከሁሉም አነሳለሁ ብሎ የሚሞክር ሰው ለሌላው ሰው አቋራጭ ይሆናል፡፡ሌላው ሰው ያን የሚያክል ጠረጴዛ ላለመዞር ከሱ ስለሚያነሳ! አንዷ ሴትዮ ዞረው ዞረው ሊጨርሱ ትንሽ ሲቀራቸው እያለከለኩ ‹‹ባጃጅ ቢኖር እንዴት ጥሩ ነበር›› ብለዋል አሉ፡፡ . ሠርግ ላይ ያየኋት ኢክራም ሌላ ሆነችብኝ፡፡ግን ኢማን ስላላት ለዚህም መልስ ይኖራታል ብዬ አጨብጭቤ ዳርኳት፡፡ የሠርጓ ዕለት ለትዳር ጠይቋት እንቢ ያለችው ሙዓዚን እንደወትሮው አዛን ሳያወጣ ቀረ፤አባቷ አክብረው ሠርጉን ቢጠሩትም አልመጣም፤መስጊድም አልታየም፤ግን. . . እሱም ኢማን አለው፡፡ . ከጋብቻዋ በኋላ ከባሏ ጋር መኖር ጀመረች፡፡ባሏ ‹‹ኢማን አለው›› ብትልም መስጊድ አይተነው አናውቅም፡፡ግን ሰው ሁሉ ኢክራምን ያምናታል፡፡ባሏ ጁምዓ ዕለት ዙህር ይሰግዳል፣ረመዳን ሲደርስ ይፆማል፤ከሰዎች ጋር ሲሆን ይሰድቃል፤የተቀደደበትን ልብስ ለምስኪን ይሠጣል፤ብቻ. . . ኢክራም ያገባችው መኪና ስላለውና፣ድርጅቶች ስላሉት ወይም ውጪ ስለሚመላለስ አይደለም፣ኢማን ስላለው ነው፣ኢማን ባይኖረው ኢክራም መች ታገባው ነበር? ዋናው ኢማን ነው! . ኢክራምም ከሠርግ በኋላ ቅጥነቷ መጥፋት ጀመረ፤ሰፈር ውስጥ አትታይም፤ሱቅ እንኳ የቀጠረቻቸው ሠራተኞች ናቸው የሚሄዱላት፡፡ለቅሶ አትደርስም፤ሠርግ አትሄድም፤ ቤተሰቦቿን እንኳ ለዒድ ነው የምትጠይቀው፤ ምክንያት ሳይኖራት እንዲህ አታደርግም! ምክንያቱም ኢክራም ኢማን አላት፡፡ . የሚገርመው የኢክራም ትዳር ብዙ አልተራመደም፤ከሁለት ዓመት በኋላ ባሏ ፈታት፡፡ሠርጋቸው ሸሪዓዊ ባይሆንም ትዳራቸው በሸሪዓው ሕግ መሠረት ስለነበር ባል በቃኝ ብሎ ፈታት፡፡ከማልቀስ ውጪ ኢክራም ምንም ማድረግ አልቻለችም፡፡ምክንያቱም ኢክራም ኢማን አላት! . ባል ምክንያቱን ሲጠየቅ ‹‹አታምነኝም፤በዚያ ላይ በጣም ትቀናለች!›› አለ፡፡ ‹‹ሁልጊዜ ማታ ዒሻ ላይ ደውላልኝ የት ነህ ስትለኝ ‹‹መስጊድ ነኝ!›› ስላት አታምነኝም፡፡ ‹‹መስጊድ ከሆንክ ኢማሙን አገኛኘኝ!›› ትለኛለች›› አለ፡፡ እኔ ኢክራምን ከትዳር በፊት አውቃታለሁ! የትዳር መሥፈርቷን አውቃለሁ፤ካገባች በኋላም ብትጠፋብኝም ጉዳይዋን ሁሉ እከታተላለሁ፤ስለሷ አወራለሁ፡፡ምክንያቱም ኢማን አለኝ! . ይሄን ወሬ ሰብስቤ ለሰዎች ስናገር፣ስተረተር ይሰሙኛል፤እነሱን ለማሳቅ ብዬ ሰው ስቦጭቅ ይሰሙኛል! ለምን? ኢማን ስላላቸው፡፡ ትዳር ፖለቲካ ሆኗል፤የሚጋቡት እንደ ኢክራምና ባሏ ያሉ ሰዎች ናቸው፡፡ወንዱ ሁሉ መርካቶ ገብቶ ነጋዴ የሆነው ለም ይመስልሃል? ትምህርቱን አቋርጦ ንግድ ውስጥ የሰመጠው ለምንድነው? ብዙ ሴቶች እንደሚሉት ‹‹ኪሱ ውስጥ ኢማን ለመሙላት ነው!›› . እንደ ድሮ አባቶቻችንና እናቶቻችን ሲጠቀሙበት የነበሩት የትዳር መስፈርቶች ቀሩ፤አሁን ጥያቄው ‹‹ያኖረኛል ወይ? አኖራታለሁ ወይ?›› ማደጎ ይመስል የሕልውና ጥያቄ ብቻ! ወንዱም ተሰቃየ፣ በሠላሳ ዓመቱ መሸበት ጀመረ! . ባየሁትና በሰማሁት መሠረት አንድ ሚስጥር ልናገር ‹‹ሁሉም ሰው ከኢማን ጋር ነው የሚወለደው፤ሁላችንም ኢማን አለን፤ግን አጠቃቀሙን ጥቂቶች ናቸው የሚያውቁት!›› . "በቀለም ጠብታ፣ማንነት ሲረታ!" . @tebeb @tebeb
የጥበብ ቤት: post #680 — TG.ME
March 1, 2020 9.1K 54