ነሐሴ ፪ /2/ በዚች ቀን መኑፍ ከሚባል አገር ቅድስት አትናስያ አረፈች። የዚችም ቅድስት ወላጆቿ ባለጸጎች… — ሥላሴን አመስግኑ media ✨ — TG.ME

ነሐሴ ፪ /2/


በዚች ቀን መኑፍ ከሚባል አገር ቅድስት አትናስያ አረፈች። የዚችም ቅድስት ወላጆቿ ባለጸጎች ነበሩ እነርሱም በሞቱ ጊዜ  እንግዶችን እና የገዳም አባቶችን ሁሉ ትቀበላቸው ነበር።

ከዚህም በኋላ ክፉ ሰዎች ወደ ኃጢአት መለሷትና ኃጢአት መስራት ጀመረች። ስለዚህም ነገር የገዳም አባቶች ሰምተው ዮሐንስ ሐጺርን በንስሐ እንዲመልሳት ላኩት። እርሱም ወደርሷ በገባ ጊዜ በዝሙት ልትጥለው አልጋዋ ላይ ሆና ጠበቀችው። እርሱም እንዲህ እያለ ይዘምር ነበር በሞት ጥላ ውስጥ ብሔድም እንኳ ክፉን አልፈራውም አንተ ከእኔ ጋራ ነህና።

ከእርሷ ጋራም በአስቀመጠችው ጊዜ ራሱን ዘንበል አድርጎ አለቀሰ መነው ብትለው እግዚአብሔርን እንዳሳዘነችው ነገራት። በመጨረሻም ቃሉንም ሰምታ ደነገጠችና ተንቀጠቀጠች ምን ይሻለኛል አለችው ንስሐ ግቢ አላት እርሷም እግዚአብሔር ይቀበለኛልን አለችው እርሱም አዎን አላት እርሷም ወደምትሔድበት ከአንተ ጋራ ውሰደኝ አለችው እርሱም ነዪ ተከተይኝ አላቴና ተከተለችው።

በመሸ ጊዜም እርሷን አስተኝቶ እርሱ ግን በጸሎት ይተጋ ነበር። ሌሊትም በጸሎት ላይ ሳለ የብርሃን ምሰሶ አየ መላዕክትም የአንዲትን ነፍስ ሲያሳርጉ አየ። በነጋም ጊዜ ወደ አትናስያ ሲደርስ ሞታ አገኛት። ስለ ርሷም ያስረዳው ዘንድ እየሰገደ ወደ እግዚአብሔር ለመነ። እግዚአብሔርም ገና ቤቷን ትታ ስትወጣ ይቅር እንዳላት ነገረው።

ከዚህም በኋላ ሒዶ ለአረጋውያን የሆነውን ሁሉ ነገራቸው እነርሱም እርሱ እንዳያት ማየታቸውን ነገሩት የኃጢአተኛን ወደ ንስሐ መመለሱን እንጂ ሞቱን የማይሻ እግዚአብሔርን አመሰገኑት።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ምንጭ:- መጽሐፈ ስንክሳር
❤3
August 8, 2026 378