ሰኞ
ጳጉሜ 2
Sep 7
መነሳሳት
2ኛ ቆሮንቶስ 8፡1፣ 5 እና 2ኛ ቆሮንቶስ 9፡7፣ 9፣ 13፣ 15ን አንብቡ። የእነዚህ ክፍሎች ማዕከላዊ መልእክት ምንድን ነው?
የመስጠት ቋንቋ በ2ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 8 እና 9 ውስጥ ተንሰራፍቶ ይገኛል፦ “የእግዚአብሔር ጸጋ... ተሰጥቶአል” (2ኛ ቆሮ. 8፡1)፤ “ራሳቸውን ሰጡ” (2ኛ ቆሮ. 8፡5)፤ “እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና... እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ” (2ኛ ቆሮ. 9፡7)፤ “ለድሆች ሰጠ” (2ኛ ቆሮ. 9፡9)፤ “ስለ ስጦታችሁ ልግስና... እግዚአብሔርን ያከብራሉ” (2ኛ ቆሮ. 9፡13)፤ “ስለማይነገር ስጦታው ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን” (2ኛ ቆሮ. 9፡15)። ሁለቱ ምዕራፎች የሚጀምሩትም የሚጨርሱትም በመስጠት ቋንቋ ነው (2ኛ ቆሮ. 8፡1 እና 2ኛ ቆሮ. 9፡15)። እነዚህን ሁለት ምዕራፎች ስናነብ የመስጠትን ሐሳብ በአእምሮአችን መያዝ አለብን። ክፍሎቹ መባ ለመስጠት ቢያንስ አራት ዋና ዋና ምክንያቶችን ያቀርባሉ፦
ለእግዚአብሔር ጸጋ ያለን ምስጋና (2ኛ ቆሮ. 8፡1፤ 2ኛ ቆሮ. 9፡14፣ 15)፦ 2ኛ ቆሮንቶስ 8–9 የሚጀምረው “ስለ እግዚአብሔር ጸጋ” በመጥቀስ ነው (2ኛ ቆሮ. 8፡1)። በመቀጠልም ጳውሎስ “የጌታችንን የየሱስ ክርስቶስን ጸጋ አውቃችኋልና” ይላል (2ኛ ቆሮ. 8፡9)። እዚህ ጋ የእግዚአብሔርና የክርስቶስ ጸጋ መባ ለመስጠት እንደ ቀዳሚ ምክንያት ቀርቧል። እግዚአብሔር ክርስቶስን በመስጠት ለእኛ ብዙ አድርጎልናል። እኛም በምላሹ ስጦታዎቻችንን ስናቀርብ፣ በሕይወታችን ውስጥ ያለውን የእግዚአብሔርን ጸጋ ዕውቅና እንሰጣለን። ልክ እንደ መስጠት ሐሳብ ሁሉ “ጸጋ” (charis) የሚለው ቃልም
በምዕራፍ 8–9 ውስጥ በተደጋጋሚ ተጠቅሷል። ጳውሎስ በሕይወታችን ውስጥ ያለው የክርስቶስ ጸጋ ለሌሎች ወደሚተርፍ ጸጋና ወደ ምስጋና እንደሚመራ ለማሳየት ይህን ቃል በተለያዩ ትርጉሞች ይጠቀምበታል።
የየሱስን አርአያነት የመከተል ፍላጎት (2ኛ ቆሮ. 8፡9)፦ የሱስ ባለጠጋ ነበረ ነገር ግን ደሃ ሆነ (እነዚህ ቃላት እርሱ ከዘላለም የነበረውን አምላክነቱንና ከዚያም ወደ ሰውነቱ መምጣቱን የሚያሳዩ ምልክቶች መሆናቸውን ያስታውሱ)። ይህ ሊሆን የቻለበት አንድ መንገድ ብቻ ነው፤ እርሱም ሁሉንም ነገር መስጠቱ ነው። እኛም እንዲሁ መባችንን በማካፈል ሌሎች ክርስቶስን እንዲያውቁ መንገድ እንከፍታለን።
የእግዚአብሔርን በረከቶች የማካፈል ፍላጎት (2ኛ ቆሮ. 9፡10፣ 11)፦ ለሌሎች የምንሰጠው በመጀመሪያ ከእግዚአብሔር ስለተቀበልን ብቻ ነው። ለጋሶች እንድንሆን እርሱ ባለጠጋ ያደርገናል።
እውነተኛ ፍቅር (2ኛ ቆሮ. 8፡8፣ 24)፦ መስጠት የእውነተኛና የቅን ፍቅር መፈተኛ ነው። ፍቅር በአንድ ሰው ልብ ውስጥ ለመኖሩ ትልቁ ማስረጃ ነው። በአጭር አነጋገር፣ ፍቅራችሁን በተግባር (በገንዘባችሁ) ግለጡ ማለት ነው። ለጋስነታችሁ ምን ያህል ነው? ከመስቀሉ ብርሃን አንጻር፣ ልትሰጡ ከምትችሉት አንጻር የምትሰጡት ምን ያህል ነው?