በሙሽራዋ ዕርገት የሙሽሪት ቤተ ክርስቲያን ደስታ 📖 በመጋቤ ሐዲስ ዶ/ር ሮዳስ ታደሰ 📚 ነገረ ክርስቶስ… — መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ (ዶክተር) Dr Rodas Tadese — TG.ME

በሙሽራዋ ዕርገት የሙሽሪት ቤተ ክርስቲያን ደስታ
📖 በመጋቤ ሐዲስ ዶ/ር ሮዳስ ታደሰ
📚 ነገረ ክርስቶስ መጽሐፌ ገጽ 209-212

☁️ ቅዱስ ሉቃስ እንደጻፈው ጌታችን በሚያርግበት ጊዜ ሐዋርያት ወደ ሰማይ በናፍቆት ሽቅብ ሽቅብ ትኲር ብለው ሲመለከቱ ነጫጭ ልብስ ለብሰው መላእክት ተገልጠውላቸዋል።

📖 የሐዋ ፩፥፲

🤍 ነጫጭ ልብስ ለብሰው መታየታቸው በትንሣኤው እንደተገለጡት “ወርኀ ፍሥሐ፣ ወርኀ ተድላ” ነው ሲሉ ነው።

🕊️ ከዚያም፦
“የገሊላ ሰዎች ሆይ ወደ ሰማይ እየተመለከታችኊ ስለ ምን ቆማችኋል? ይኽ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲኼድ እንዳያችኹት እንዲኹ ይመጣል” ብለው በናፍቆት ሲያዩት ለነበሩት ለሐዋርያት ጉባኤ ዳግመኛ ለፍርድ ተመልሶ የመምጣቱን ነገር ነግረዋቸዋል፡፡

በጌታችን ዕርገት የተደረገው የመላእክትና የሐዋርያት ጉባኤ፣ የቤተ ክርስቲያን አንድነት፣ የሰጠውን ፍጹም ደስታና ሐሴት ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ የቤተ ክርስቲያንን የምእመናንን አንደበቷን አንደበት አድርጎ አምልቶና አስፍቶ እንዲኽ ይተነትነዋል፦

☞ “የገነነው ሙሽራ በአባቱ ቤት ይመሰገናል፤ የብርሃን ልጆች ጉባኤም በርሱ መኼድ ተቀሰቀሱ፤ ሙሽሪት፣ የሐዋርያት ጉባኤ፣ ቤተ ክርስቲያን፣ ሙሽራዋ በታላቅ ክብር ሲያርግ ተመለከተች፤ መከራ ሲቀበል አይታ አጐንብሶ የነበረውን ራሷን ቀና አደረገች፤ በኀይል ተነሥቶ ወደ አባቱ ያረገውን ተመለከተች፤ እናም በሞቱ የተነሣ በሐዘን ተቀስፎ የነበረ ልቧ ተጽናና 📖 ዮሐ ፲፬፥፳፰-፳፱።

💒 የሙሽሪት ናፍቆት
☁️ በአየር ላይ ሲኼድ ስታይ በስቅለቱ ጊዜ የደረሰበትን ስድብና ውርጅብኝን ተወች፤ ከርሱ ፊት የሚጋልቡትን ደመናዎችና ጒምን ተመለከተች፤ እናም ርሱን ተከትላ የብርሃን ልጅ እንደመኾኗ ለመኼድ ተመኘች።

❤️ “ወደምትኼድበት ከአንተ ጋር ውሰደኝ፤ የአንተ ኾኜያለኹና፤ ወደ አባትኽ ካንተ ጋር ላርግ ፈቃድኽ ይኹን” አለችው።

✝️ በፍቅርኽ ፈለግኸኝ፤ በመከራኽ ዐጨኸኝ፤ በጦር ተወግተኽ ነጻ አወጣኸኝ፤ እነሆ ገንነኻል፤ አንተን ተከትዬ ወደ አባትኽ ቤት ልሩጥ።

🌹 ወደ ሸንጎው ውስጥ የአንተን መከራ ለማየት ገባኊ፤ በአንተ የተነሣ ከአይሁድ ኀፍረትን ተቀብዬያለኊ፤ በመስቀል ላይ ሲዘባበቱብኽም እሞት ይኾን ብዬ ፈርቼ ነበር፤ በኀጢአተኞች ስትደበደብ ሸሽቼ ተደብቄ ነበር። 📖 መሓ ፭፥፯

🪦 በወንበዴዎች መኻከልም ሲሰቅሉኽ ከአንተ ጋር ተዘባብተውብኝ ነበር፤ እንደገናም እንደ ሙታን በመቃብር ውስጥ ሲያኖሩኽ አሞኝ ነበር፤ ዕጹብ ድንቅ በኾንኸው ባንተ የተነሣ ተጽናንቼ ሐዘኔን ረሳኹት።

🕊️ በአንተ የተነሣ መሳደድ ደርሶብኛልና ከአንተ ጋር ልኺድ፤ ስምኽ ለእኔ የሚያስደስተኝ የከርቤ ዘይት ይኹንልኝ። 📖 መሓ ፩፥፫

🍷 ምሕረትኽ ከወይን የተሻለ ነውና በአንተ ልጽናና፤ ከአንተ ከሙሽራው ከምወድድኽ ጋር ወደ ቦታኽ ልኺድ፤ ጠፍቼ እንዳልቀር በአንተ እሰበሰብ ዘንድ በመንጋኽ ውስጥ ዐስበኝ።
📖 መሓ ፩፥፯

👑 በፍቅሩ የታመመች ሙሽሪት

🌸 የኢየሩሳሌም ቆነጃጅት ሆይ ንጉሡን ሙሽራ ወዴት አያችኹት? በጣም አብዝቼ ብፈልገውም ወደ ቦታው በማረጉ ፈጽሞ ላገኘው አልቻልኩም። 📖 መሓ ፫፥፪

💘 እነሆ በሙሽራው ፍቅር ታምሜያለኊ ርሱንም እፈልገዋለኊ፤ ከኹሉም ውቦች በላይ ውብ የኾነውን እወድደዋለኊ፤ ሲናገር ከናፍሮቹ መውደድን ያዘንባሉ፤ ለሚመለከቱት ኹሉ ርሱ ከኹሉም በላይ ውብ ነው።
📖 መዝ ፵፬፥፪

🌿 ልብሶቹም ልክ እንደ አሮን ጣፋጭ የዕጣን መዐዛን ይረጫሉ፤ ከርሱ የሚፈስሰውም ነጭና ቀይ፤ ውሃና ደም ነው።
📖 መሓ ፭፥፲፤ ዮሐ ፲፱፥፴፬

🌺 ለሚመለከተው ጉንጮቹ የሽቱ ብልቃጥ ናቸው፤ አባቱ በርሱ ምክንያት ዓለምን በመታረቁ ሙሉ በሙሉ ሽቱ ነው።

☁️ ወደ ሰማይ ያረገው ሙሽራ

👣 በመንገድ ላይ አግኝቶኝ ነበር ባለማወቄ የተነሣ አላወቅኹትም ነበር። 📖 ሉቃ ፳፬፥፲፮

☁️ ወደ ሰማያቱ ዐርጓል፤ ርሱን አየው ዘንድ ርሱ ወዳለበት ማን ያሳርገኛል? አለች።

⛰️ የሐዋርያት ጉባኤ በደብረ ዘይት ቆመዋል፤ ድንግል ሙሽሪት፣ ቤተ ክርስቲያን፣ ምእመን፣ ከምድር ያረገውን ሙሽራ አተኲራ ትመለከተዋለች። 📖 የሐዋ ፩፥፲

🕊️ እነሆ ርሱ ትቷት በማረጉ የተነሣ ልታነባ ስትል መላእክት “እነሆ እንደገና ይመጣል” ብለው ሊያጽናኗት ቀረቧት።
📖 የሐዋ ፩፥፲፩

👑 ንግሥቲቱ ሙሽሪት፣ ቤተ ክርስቲያንን፣ ምእመንን፣ የንጉሡ አገልጋዮች (መላእክት) ሲያጽናኗት ነበር።

“ከቶ ማዘን የለብሽም ምክንያቱም ይኸው ሙሽራ ይመጣልና በርግጠኛነት ታይዋለሽ፤ የኼደው የከበሩ ነገሮችን ይዞልሽ ሊመለስ ነው፤ ፈጽሞ አይተውሽም፤ ወደ አንቺም ይመለሳል።”

🕊️ “የሚመጣውን ተመልከቺው፤ በአካሉ ተሸከመሽ እነሆ በርሱ የተቀደሰ ስፍራ ከርሱ ጋር ነሽ፤ መንፈሱን ሰጠሽ።”
📖 ዮሐ ፳፥፳፪

💛 “እነሆ ርሱ እዚኹ ከአንቺ ስፍራ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ ራስሽ በርሱ ተፈጠርሽ፤ ርሱ ግን ከአንቺ ጋር ነውና መቼም ብቻሽን አይተውሽም።” 📖 ዮሐ ፲፬፥፲፰

🌍 ሰማይና ምድር በዕርገቱ ተጣመሩ

🤍 መላእክት ደቀ መዛሙርትን ከብበው አበረታቷቸው፤ “ጌታችኊ ይመጣል፤ ርሱ ምስጉን ነውና ፈጽሞ ዐትዘኑ፤ ወደ ሰማይ ሲኼድ እንዳያችኹት እንዲኹ ሲመጣም ታዩታላችኊ፤ ዳግመኛ በክበበ ትስብእት እያበራ ይመጣልና” አሏቸው።

🕊️ መላእክቱ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ለመደሰት መጡ፤ አንዳቸውን ጉባኤ ከሌላቸው ጋር በታላቅ ሰላም አጣመረ፤ ከደስታቸው የተነሣ መላእክት ራሳቸውን በነጭ ካባዎች አጐናጸፉ።

ምክንያቱም በጠላትነት ከነበሩ ከሰው ዘሮች ጋር አስታርቋቸዋልና፤ በእግዚአብሔር ልጅ ሰማይና ምድር ርስ በርስ ተጣመሩ፤ በርሱ አማካይነት በሰው ዘርና በመላእክት መኻከል ሰላም ሰፈነ።

🔥 የወልድ መገለጥ እና የሰማያውያን ድንቅ

👼 የሰማያዊ ፍጥረታት ነገዶች ርሱን ሊያዩ ፈለጉ፤ ምክንያቱም ወደ እኛ መጥቶ ሥጋን ለብሶ በመኻከላችን እስኪኖር ድረስ አላዩትም ነበር።

☀️ ከአባቱ ጋር እንደነበረና ከርሱም ጋር ኅቡዕ እንደኾነ ያውቁታል፤ ነገር ግን ሰማያዊ ነገዶች ርሱን በባሕርዩ ለማየት ችሎታ አልነበራቸውም።

✝️ ለሰው ልጅ ባለው ፍቅር ሥጋን ተውሕዶ በምድር ላይ ሲገለጽ፤ ርሱ ከመገለጹ የተነሣ እነሆ የሰማይ ጭፍሮች ሊያዩት ፈለጉ፤ ኀይላት ሥልጣናት በየነገዳቸው ተደነቁ።

🌟 ምክንያቱም ስዉር የኾነው ርሱ በፈቃዱ ይመለከቱት ዘንድ ተገልጧልና፤ ወደ ሰማያት ሲያርግ ሥልጣናት ሊያዩት ተሰበሰቡ፤ ምክንያቱም ይዞት በመጣው የምሥራች ተነሳሥተው እና ተቀስቅሰው ለርሱ ምስጋናን አቀረቡለት።

🕯️ ርሱ ራሱ እንዲገለጽ የወደደው ዐዲስ ተአምር፣ ምስጢር ያውም የወልድን መገለጥ በቅንነት ለማየት ፈለጉ፤ በሥጋ ተገለጸ፤ በክብርም ዐረገ፤ ሲያርግም በሰዎችና በመላእክት ታየ። 📖 ፩ኛ ጢሞ ፫፥፲፮

📚 ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ በእንተ ዕርገተ እግዚእ
በመጋቤ ሐዲስ ዶ/ር ሮዳስ ታደሰ
📚 ነገረ ክርስቶስ መጽሐፌ ገጽ 209-212
[ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ በዕርገትኽ ዕርገታችንን የገለጽክልን እንወድኻለን]
❤239🥰23👍13👏2
May 20, 2026 34K 75