በዓመቱ የ2018 ዓ.ም. የመጨረሻዋ ሙሉ ጨረቃ የሚታይ ከፊል የጨረቃ ግርዶሽ በኢትዮጵያ ከመጋቤ ሐዲስ ዶክተር… — መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ (ዶክተር) Dr Rodas Tadese — TG.ME

🌕🌑 በዓመቱ የ2018 ዓ.ም. የመጨረሻዋ ሙሉ ጨረቃ የሚታይ ከፊል የጨረቃ ግርዶሽ በኢትዮጵያ
ከመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ
🔭 ሳይንሳዊ፣ 📖 መጽሐፍ ቅዱሳዊና 🇪🇹 የኢትዮጵያ ሥነ ፈለክ እይታዬ

💥 ባለፈው ዓመት 2017 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የዓመቱ መጨረሻ የመጨረሻዋ ሙሉ ጨረቃ ጳጉሜን 2 ከምሽቱ 2 ሰዓት ሙሉ የጨረታ ግርዶሽ በአድናቆት አይተናል።

🌓 በዚህም 2018 ዓ.ም በድጋሚ የነሐሴ 22 ማለዳ (ሊነጋጋ) በ2018 ዓ.ም. የመጨረሻዋ ሙሉ ጨረቃ ዕለት ከፊል የጨረቃ ግርዶሽ (Partial Lunar Eclipse) ይታያል።

በተለይ ይህ ግርዶሽ የሚያስደንቀው በከፍተኛው ደረጃ ጨረቃዋ ሙሉ በሙሉ ሳትጋረድ እስከ 96% ገደማ የሚሆነው ክፍሏ በምድር ዋና ጥላ ውስጥ መግባቱ ነው።
🌓 ለአንባብያን በተራ ቁጥር ጥቂት ለመጻፍ ያህል:-

🌍 1. የጨረቃ ግርዶሽ ምንድን ነው?

☀️ ፀሐይ 🌍 ምድር 🌕 ጨረቃ

በአንድሮሜዳ መጽሐፍ ላይ በስፋት እንደተጻፈው የጨረቃ ግርዶሽ የሚፈጠረው ምድር በፀሐይና በጨረቃ መካከል ስትገባ ነው።

ፀሐይ ብርሃኗን ወደ ጨረቃ ትልካለች፤ ነገር ግን ምድር በመካከል ስትገባ የምድር ጥላዋ በጨረቃ ላይ ያርፋል።

🌑 የምድር ጥላ ኹለት ዋና ክፍሎች አሉት፦

🔸 Penumbral Shadow ደብዛዛው የውጭ ጥላ
🔸 Umbral Shadow ጥቁሩና ዋናው ጥላ

ጨረቃ ከፊል ክፍሏን ወደ Umbra ስታስገባ Partial Lunar Eclipse ከፊል የጨረቃ ግርዶሽ ይባላል።

ስለዚኽ በስፋት ለማወቅ የኢትዮጵያ የከዋክብት ሊቃውንት የተራቀቁበትን "ትርጓሜ ሚጠተ ብርሃናት ዘሔኖክ" መጽሐፍ አንብቡ።

🇪🇹 2. የዚህ ግርዶሽ መጀመሪያውን ከኢትዮጵያም ማየት ይቻላል።

🌘 ዛሬ ሊነጋጋ በኢትዮጵያ ሰዓት ሌሊት 10:23 ወይም በፈረንጆች 4:23 አካባቢ Penumbral ግርዶሽ ይጀምራል።

🌑 ሊነጋጋ 11:33 ወይም (5:3 አካባቢ የሚታየው ከፊል ግርዶሽ ይጀምራል።

🌅 12:17 ጠዋት (6:17) ጠዋት አካባቢ ጨረቃ በአዲስ አበባ ትጠልቃለች።

ስለዚህ በኢትዮጵያ የምናየው የግርዶሹን መጀመሪያ ክፍል ብቻ ነው፤ የግርዶሹ ዓለም ዐቀፍ ከፍተኛ ደረጃ ሲደርስ ጨረቃዋ በአዲስ አበባ ከአድማስ በታች ትሆናለች።

👁️ የሚመከረው የመመልከቻ አቅጣጫ፦ ምዕራብ ደቡብ ምዕራብ

⛰️ ሕንፃና ተራራ ያልጋረደው የምዕራብ አድማስ ያለው ከፍ ያለ ቦታ የተሻለ ነው።

🌑 ይህ ግርዶሽ ሙሉ የጨረቃ ግርዶሽ (Total Lunar Eclipse) አይደለም።

ነገር ግን ጨረቃዋ በጣም ጥልቅ ምድር ጥላ ስለምትገባ፣ በከፍተኛው ደረጃ 96% ገደማ የሚሆነው የጨረቃ ዲስክ በምድር ዋና ጥላ ውስጥ ይሆናል።

🌕➡️🌖➡️🌗➡️🌘

በመሆኑም በዓይን ሲታይ ወደ ሙሉ ግርዶሽ በጣም የቀረበ ይመስላል።

🔴 4. “የደም ጨረቃ” ለምን ትባላለች?

በጨረቃ ግርዶሽ ጊዜ ጨረቃ አንዳንድ ጊዜ ቀይ፣ መዳብማ ወይም ብርቱካናማ መልክ ልትይዝ ትችላለች።

ይህ የሚፈጠረው ብርሃን በምድር ከባቢ አየር ሲያልፍ ነው።

🌍 የምድር ከባቢ አየር አጭር ሞገድ ያለውን ሰማያዊ ብርሃን በብዛት ይበትናል፤ ቀይና ብርቱካናማ ብርሃን ግን ወደ ምድር ጥላ ውስጥ ተጣምሞ ሊደርስ ይችላል።

ይህ በሳይንስ Rayleigh scattering ከሚባለው የብርሃን መበተን ጋር የተያያዘ ነው።

🌅 ፀሐይ ስትጠልቅ ሰማዩ ቀይ የሚመስለውና በጨረቃ ግርዶሽ ጨረቃ ቀይ የምትመስለው ተዛማጅ የብርሃን ሂደት ነው።

📖 5. ጨረቃ፣ ፀሐይና ከዋክብት በመጽሐፍ ቅዱስ

መጽሐፍ ቅዱስ ፀሐይን፣ ጨረቃንና ከዋክብትን በተደጋጋሚ ይጠቅሳል።

«“እግዚአብሔርም ሁለት ታላላቅ ብርሃናትን አደረገ፤ ታላቁን ብርሃን ቀንን እንዲገዛ፥ ታናሹንም ብርሃን ሌሊትን እንዲገዛ።”
✠ ዘፍጥረት 1፥16»

እንዲሁም፦

«“ለምልክቶችና ለዘመናት፥ ለዕለታትና ለዓመታትም ይሁኑ።”
✠ ዘፍጥረት 1፥14»

ይህ ክፍል የሰማይ ብርሃናት ቀን፣ ዘመንና ዓመትን ለመለየት እንደሚያገለግሉ ያሳያል።

🌕 6. “ጨረቃ ወደ ደም እንደምትለወጥ”

በነቢዩ ኢዩኤል፦

«“ፀሐይ ወደ ጨለማ፥ ጨረቃም ወደ ደም ትለወጣለች፥ ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ሳይመጣ።”
✠ ኢዩኤል 2፥31»

ይህንኑ ቃል ቅዱስ ጴጥሮስ በሐዋርያት ሥራ ይጠቅሳል፦

«“ፀሐይ ወደ ጨለማ፥ ጨረቃም ወደ ደም ትለወጣለች።”
✠ ሐዋርያት ሥራ 2፥20»

⚠️ ነገር ግን አንባብያን በእዚህ ላይ ጥንቃቄ ያስፈልጋል።

እያንዳንዱን የጨረቃ ግርዶሽ “ይህ የኢዩኤል ትንቢት ፍጻሜ ነው” ብሎ መወሰን አይገባም።

መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን ምስሎች በትንቢታዊና በፍጻሜያዊ ዐውድ ይጠቀምባቸዋል፤ የጨረቃ ግርዶሽ ደግሞ በሥነ ፈለክ ሕግ ሊሰላና አስቀድሞ ሊታወቅ የሚችል የተፈጥሮ ክስተት ነው።

7. ሰማያት የፈጣሪን ሥራ ይናገራሉና ግርዶሽን መመልከት ፍርሃት ብቻ የሚፈጥር ነገር መሆን የለበትም። የፍጥረትን ሥርዓትና ድንቅነት ለማሰብም ዕድል ነው።

«“ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፤ ጠፈርም የእጆቹን ሥራ ያወራል።”
✠ መዝሙር 19፥1»

☀️ ፀሐይ
🌍 ምድር
🌕 ጨረቃ

በተወሰነ ሥርዓት መጓዛቸው የሰማይ አካላት እንቅስቃሴ በሕግና በሥርዓት መሆኑን ያሳያል።

🇪🇹 8. ጨረቃና የኢትዮጵያ የዘመን የሥነ ፈለክ እውቀት

ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ከፀሐይ፣ ከጨረቃ፣ ከከዋክብትና ከዘመን አቆጣጠር ጋር የተያያዘ ረጅም ታሪክና ዕውቀትና ሀብት አላት። ከ88ቱ ሕብራተ ከዋክብት ውስጥ እንደ ሀገር ለ3 ጊዜያት የተጠቀሰችው ኢትዮጵያ ብቻ ናትተ

በቤተ ክርስቲያንም የበዓላት አቆጣጠር፣ በፀሐይም በጨረቃም ይለካሉና የባሕረ ሐሳብ ስሌት ትልቅ ቦታ አለው።

ስለዚህ የሰማይ አካላትን መመልከት ለአባቶቻችን የማይታወቅ ነገር አልነበረም፤ ዘመንን ለመለየት፣ ወራትን ለማስላትና የበዓላትን ጊዜ ለመወሰን የሥነ ፈለክ ምልከታና ስሌት ከዘመን አቆጣጠር ጋር ተያይዞ ኖሯል። እጅግ የብዙ ብዙ የአስትሮኖሚ መጻሕፍት ጽፈውልናል። በመኾኑም ትውልዱ ይህንን ሀብቱን በሚገባ መጠበቅ ይገባዋል።

🌓 ሳይንስ በዘመናችን በብዙ የተራቀቁ መሣሪያዎች ታግዞ የሚነግረንን ግርዶሽ ቀደምቶቹ ኢትዮጵያውያን ተራቀውበት መርምረውት ጽፈውበት ኖረዋል።

👁️ 9. ግርዶሹን እንዴት እንመልከት? ለሚለው
🌑 ከፊል የጨረቃ ግርዶሽ በዓይን ማየት ደህንነቱ የተጠበቀ ነው።

☀️ የፀሐይ ግርዶሽ እንደሚያስፈልገው ልዩ eclipse glasses አያስፈልግም።

🔭 Binoculars ወይም Telescope ካለ የምድር ጥላ በጨረቃዋ ላይ ሲገባ በተሻለ ሁኔታ ለመመልከት ይረዳል።

📷 ፎቶ ለማንሳትም ከ11:30 ጠዋት በኋላ ጨረቃዋ ወደ ምዕራብ አድማስ በጣም ዝቅ ስለምትል ከፍ ያለና አድማሱ ክፍት የሆነ ቦታ ይመረጥ።

🌕🌑 10. በጨረቃ ግርዶሽ ጊዜ የምናየው በጨረቃ ላይ የወደቀውን የምድራችንን ጥላ ነው።

🌍➡️🌑

ስለዚህ ነሐሴ 22 ሊነጋጋ ሲል ማለዳ ወደ ጨረቃ ስንመለከት፣ በሌላ የሰማይ አካል ላይ የራሳችንን ዓለም ጥላ እያየን ነው።

በመጨረሻም 🌕 ነሐሴ 22 ቀን 2018 ዓ.ም.
🌑 August 28, 2026
🇪🇹 ኢትዮጵያ — አዲስ አበባ
ማለዳ ደመና ከሌለ ወደ ምዕራብ ሰማይ ተመልከቱ።

የምድር ጥላ በጨረቃ ላይ ሲገባ፣ የሰማይ አካላትን ሥርዓት ያስረዳናል፤ እምነት ደግሞ ፍጥረትን በድንቅነትና በምስጋና እንድናይ ይጋብዘናል።

«“ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፤ ጠፈርም የእጆቹን ሥራ ያወራል።”
✠ መዝሙር 19፥1»
❤77👍13👏6🔥2
August 27, 2026 4.9K 5 25