ማቴዎስ 4
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ከዚያ ወዲያ ኢየሱስ ከዲያብሎስ ይፈተን ዘንድ መንፈስ ወደ ምድረ በዳ ወሰደው፥
² አርባ ቀንና አርባ ሌሊትም ከጦመ በኋላ ተራበ።
³ ፈታኝም ቀርቦ፦ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ እነዚህ ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ በል አለው።
⁴ እርሱም መልሶ፦ ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል አለው።
⁵ ከዚህ በኋላ ዲያብሎስ ወደ ቅድስት ከተማ ወሰደውና እርሱን በመቅደስ ጫፍ ላይ አቁሞ፦
⁶ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል እግርህንም በድንጋይ ከቶ እንዳትሰናከል በእጃቸው ያነሡሃል ተብሎ ተጽፎአልና የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ፥ ወደ ታች ራስህን ወርውር አለው።
⁷ ኢየሱስም፦ ጌታን አምላክህን አትፈታተነው ተብሎ ደግሞ ተጽፎአል አለው።
⁸ ደግሞ ዲያብሎስ እጅግ ረጅም ወደ ሆነ ተራራ ወሰደው፥ የዓለምንም መንግሥታት ሁሉ ክብራቸውንም አሳይቶ፦
⁹ ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ አለው።
¹⁰ ያን ጊዜ ኢየሱስ፦ ሂድ፥ አንተ ሰይጣን ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአልና አለው።
July 9, 2024 680