ዘፍጥረት 3 ¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯ ¹ እባብም እግዚአብሔር አምላክ ከፈጠረው ከምድር አውሬ ሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ ነበረ። ሴቲቱንም፦ በውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዝዞአልን? አላት። ² ሴቲቱም ለእባቡ አለችው፦ በገነት ካለው ከዛፍ ፍሬ እንበላለን፤ ³ ነገር ግን በገነት መካከል ካለው ከዛፉ ፍሬ፥ እግዚአብሔር አለ፦ እንዳትሞቱ ከእርሱ አትብሉ አትንኩትም። ⁴ እባብም ለሴቲቱ አላት፦ ሞትን አትሞቱም፤ ⁵ ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ። ⁶ ሴቲቱም ዛፉ ለመብላት ያማረ እንደ ሆነ፥ ለዓይንም እንደሚያስጎመጅ፥ ለጥበብም መልካም እንደ ሆነ አየች፤ ከፍሬውም ወሰደችና በላች፤ ለባልዋም ደግሞ ሰጠችው እርሱም ከእርስዋ ጋር በላ። ⁷ የሁለቱም ዓይኖች ተከፈቱ፥ እነርሱም ዕራቁታቸውን እንደ ሆኑ አወቁ፤ የበለስንም ቅጠሎች ሰፍተው ለእነርሱ ለራሳቸው ግልድም አደረጉ።
July 9, 2024 669