ሁሉም ልክ ነኝ ካለ ማንም ልክ አይሆንም! ሁሉም ለራሱ 'ትክክል' ነው" የሚል ደካማ ፍልስፍና አብሮ… — መጽሐፍቶችን በpdf📚 — TG.ME

ሁሉም ልክ ነኝ ካለ ማንም ልክ አይሆንም!


ሁሉም ለራሱ 'ትክክል' ነው" የሚል ደካማ ፍልስፍና አብሮ አያኗኑርም፤ ኧረ ራስንም አያኖርም። ቢያንስ ለጋራ ጉዳይ የጋራ ልክ፣ የጋራ መለኪያና የጋራ ዳኝነትም መኖር አለበት። ባይፃፍም ባይደነገግም እንደሰው በጋራ ፀያፍ የሆነ ፣ በጋራ ህመም የሆነ ነገር አለኮ። ሁሉም ነገራችን በየጓዳ ልምዳችን ሆነ የሚተረጎመው። ሞት እዚህ ሌላ፣ እዛ ሌላ ሆኖ ይተረጎማል፤ ጦርነት፣ ልማት፣ ርሃብ፣ ጥጋብ፣ ውጤቱ አንድ ሆኖ ትርጉሙ የየቅል ሆነብን። በጋራ ማዘን፣ የጋራ አቋምና መርህ መያዝ ግራ ሆነብን። የሆነውን ነገር የምንኮንነውም ልክና ሰህተት የምንለውም በአድራጊው ማንነትና መለኪያ እንጅ በነገሩ ውጤት አልሆን አለ። የሾርባ ማንኪያው ዓይነት ነገር...

​ዶክተሩ ለአንድ ታካሚ መድኃኒት ያዝለታል። "በቀን አንድ የሾርባ ማንኪያ ብቻ ትወስዳለህ" ከሚል ሙያዊ ትዕዛዝ ጋር! በቀጣዩ ቀን ሰውየው ሆዱ ተነፋፍቶና እከክ በእከክ ሆኖ፣ ሽቅብ ቁልቁል እያዳፋው በቃሬዛ መጣ። ዶክተሩ ጠየቀ፦
​"ምን ሆኖ ነው?"
​"እርስዎ ያዘዙለትን መድኃኒት ባዘዙት መሠረት ሲወስድ እንዲህ ሆነ።"
​"በስህተት አብዝቶ ወስዶ ይሆን?"
​"ኧረ በጭራሽ ዶክተር! በሾርባ ማንኪያ አሉ፣ ሳይጨምር ሳይቀንስ በሾርባ ማንኪያ ለክቶ ጠጣ፤ ይኸው እንደውም ማንኪያውንም ይዘነዋል" ብለው የድግስ ጭልፋ የሚያክል የእንጨት ማንኪያ አሳዩት። ዶክተሩ ደነገጠ።
​"ምንድነው ይሄ? በሾርባ ማንኪያ ነበር እኮ ያልኩት!"

​"ዶክተር፤ እንግዲህ እኛ ሾርባ የምንጠጣው በዚህ ነው!!"

​ፍትህ፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ ክብር፣ ወንጀል፣ ድህነት... እንዴት ነው ሰዋዊ ከሆነው የህሊና መለኪያ ይልቅ በየራሳችን ሰፈርና ጓዳ እሳቤ፣ በተበላሸ አስተዳደግና በመሃይምነታችን የሚለካው? የተማረውም በሚሰጠን ባዕድ መስፈሪያ ከእኛ መስፈሪያ የየቅል የሚሆነው እስከመቸ? የሚዲያው መስፈሪያ ምድር ላይ ካለው የማይቀራረበው እስከመቸ? እንዴትስ ነው በምላሳችን ጫፍ የማንቀምሰውን ኮሶ ለሌላው በጭልፋ ሙሉ የምንግተው? መቼስ ነው በደል እንደ በደል፣ ፍትህም እንደ ፍትህ በራሱ ተፈጥሯዊ መጠን የሚታየው? መቼ?

©አሌክስ አብርሃም

ሁሌም ማንበብ!
👌14❤9💯3👍2
August 21, 2026 3.3K 11