"በአፍላ ትጀምራላችሁ በወረት ትተውታላችሁ። ያላወቃችሁትን ለማወቅ ትጥራላችሁ፤ የያዛችሁትን ትረግጣላችሁ፤ የረገጣችሁትን ትይዛላችሁ። ምኞታችሁ ልክ የለውም አምሮታችሁ ብዙ ነው ። የአማራችሁን ስታገኙ ወዲያው ይሰለቻችኋል ።
ተው የተባላችሁትን ትሽራላችሁ የተከለከላችሁትን ትደፍራላችሁ የተፈቀደላችሁን ችላ ትሉታላችሁ ። ቤተ መቅደስ እንዳትገቡ ብትከለከሉ ወደ ፊት ቤተ መቅደሱ በመስታወት ሠርታችሁ መቅደስ ባትገቡም እንኳን ሁሉን ከውጪ ሆናችሁ ማየት ትፈልጋላችሁ ። ሁሉን ማወቅ ትፈልጋላችሁ ፤ በአንዱም ግን አትጠቀሙበትም ። ሁሉ አላችሁ ፤ግን ባዷችሁን ናችሁ ። #_ሃይማኖት #_እንጂ #_እምነት #_የላችሁም !"
ከታሪክ ፍቅርንና ልማትን ሳይሆን ጥላቻን ለይታችሁ ትቆፍራላችሁ። ከዚያም ቀጥላችሁ የከበረ ማዕድን እንዳወጣችሁ ሁሉ በኩራት ደረታችሁን ነፍታችሁ ሳትመርጡ ሁሉን በአደባባይ ትዘሩታላችሁ፤ እናም ወደ ኋላ ስለ ታሪካችሁና ስለ ቅርሳችሁ ባሰባችሁ ቁጥር ፍርሃትና ሃፍረት ይሰማችኋል ። ስለሆነም ከኋላ ታሪካችሁና ክብራችሁ እየራቃችሁ መጣችሁ። የአሸናፊነትንና የተሸናፊነት ትርጉም በአንድ ላይ የያዙ ሃውልቶች ታቆማላችሁ።
ቅቤ ላይወጣችሁ ትናጣላችሁ። በዚህ ዓለም ጥድፊያ ታማችኋል ። ሀገራችሁን ትንቃላችሁ ፤ጥላችሁ ለመሄድ ትፈልጋላችሁ፤ ከሄዳችሁ በኋላ ደግሞ አፍታ ሳትቆዩ አገሬ ናፈቀኝ ትላላችሁ ። በቁማችሁ የናቃችሁትን የሀገራችሁን አፈር በሞታችሁ ልትለብሱት ትናፍቃላችሁ። ለሀገሬ አፈር አብቃኝ ብላችሁ በድናችሁን ልካችሁ የወገኖቻችሁን ልብ ትሰብራላችሁ። ግብዝነታችሁ መጠን የለውም ። ሁለት ሀገር እንዲኖራችሁ ትፈልጋላችሁ ፤አንዱን በደም ሌላኛውን በመታወቂያ ታስባላችሁ ። ከአንዱም ግን በአግባቡ አትኖሩም። ዘመናችሁም በምልልስና በመዋተት ያልቃል ። ምን እንደምትፈልጉ አታውቁም እናም ፍለጋችሁ አያልቅም !
© አለማየሁ ዋሴ
ሁሌም ማንበብ!
21
17
5
3
1
1August 14, 2026 4.5K 12