ለኬጂ ተማሪ ወላጆች ስለ ልጅ አስተዳደግ፣ ጤናማ የምግብ ዝግጅትና የት/ቤቱን የምግብ ዝርዝር አስፈላጊነት ዙሪያ ስልጠና ተሰጠ።
ዛሬ ህዳር 06 ቀን 2019 ዓ.ም. ለመርዋ ኬጂ ተማሪ ወላጆች በልጆች አስተዳደግ፣ ወደ ት/ቤት የሚላክ ምግብ አዘገጃጀትና ተገቢውን መጠን በተመለከተ፣ እንዲሁም ት/ቤቱ የሚያዘጋጀውን የምግብ ዝርዝር መከተል ስላለው ጠቀሜታ ያተኮረ ጠቃሚና አስተማሪ ስልጠና ተሰጥቷል።
የስልጠናው ዋና ዓላማ ወላጆች በልጆቻቸው ዕድገት፣ ጤና፣ ባህሪና ትምህርታዊ ስኬት ውስጥ ያላቸውን ወሳኝ ሚና እንዲረዱ፣ ለልጆቻቸው ተገቢና ጤናማ ምግብ እንዲያዘጋጁ እና ከት/ቤቱ ጋር በተቀናጀ መልኩ እንዲሠሩ ማገዝ ነው።
1. በልጆች አስተዳደግ ውስጥ የወላጆች ወሳኝ ሚና፡
የልጅ አስተዳደግ ማለት ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን ልጆችን በአካላዊ፣ በአእምሮአዊ፣ በስሜታዊና በማህበራዊ ዘርፍ ጤናማ ሰው ሆነው እንዲያድጉ መርዳት ነው።
በዚህ ረገድ ወላጆች ለልጆቻቸው የመጀመሪያ አስተማሪዎችና የባህሪ አርአያዎች ናቸው። ልጆች የሚያዩትን፣ የሚሰሙትንና ከወላጆቻቸው የሚማሩትን በተግባር ይተገብራሉ።
በመሆኑም ወላጆች፦
- ለልጆቻቸው ፍቅር፣ ክብርና ደህንነት የተሞላበት የቤት አካባቢ መፍጠር።
- ልጆችን በትዕግሥት ማዳመጥና ስሜታቸውን መረዳት።
- ተማሪዎች ላይ አላስፈላጊ ጩኸት መሸነስ ብሎም ማስቀረት።
- በጥሩ ባህሪ፣ በንጽህና፣ በኃላፊነትና በሥነ-ምግባር ረገድ አርአያ መሆን።
- የልጆችን ዕድሜና የእድገት ደረጃ የሚመጥኑ የዕለት ተዕለት ልምዶችን ማዳበር።
- ለትምህርታቸው ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ ማድረግ።
- ልጆችን በራሳቸው እንዲተማመኑ፣ እንዲወስኑና ኃላፊነት እንዲሸከሙ ማበረታታት።
2. ወደ ት/ቤት የሚላክ ምግብ አዘገጃጀትና ጥራት፡
በተማሪዎች አካላዊ ዕድገት፣ የአእምሮ ብቃት፣ ትኩረትና የትምህርት ተሳትፎ ውስጥ ተገቢ የሆነ ምግብ ከፍተኛ ሚና አለው። በተለይም በኬጂ ደረጃ ያሉ ሕፃናት ለዕድገታቸው የተለያዩ ንጥረ ምግቦችን በተመጣጠነ መልኩ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል።
ስለዚህ ወላጆች ለልጆቻቸው ምግብ ሲያዘጋጁ የሚከተሉትን መርሆዎች መከተል ይገባል፦
- ንጹህና በጥራት የተዘጋጀ ምግብ መላክ።
- አትክልት፣ ፍራፍሬ፣ እህል፣ ፕሮቲንና ሌሎች ጠቃሚ የምግብ ዓይነቶችን ማካተት።
- ከመጠን በላይ ስኳር፣ ጨውና ዘይት የተጨመረባቸውን ምግቦች መቀነስ።
- የታሸጉ ምግቦች ፈፅሞ አለመጠቀም።
- በተቻለ መጠን ከልጁ ዕድሜ ጋር የሚስማማና ለመመገብ ቀላል የሆነ ምግብ ማዘጋጀት።
- ምግቡን በንጹህና ተገቢ የምግብ ማስቀመጫ ዕቃ ማሸግ።
- የልጆችን የአለርጂ ሁኔታና ልዩ የጤና ፍላጎቶች ግምት ውስጥ ማስገባት።
3. ወደ ት/ቤት የሚላክ ምግብ ተገቢ መጠን፡
ለሕፃናት ምግብ ሲዘጋጅ ጥራቱ ብቻ ሳይሆን መጠኑም እጅግ አስፈላጊ ነው። ከልጁ የምግብ ፍላጎትና የዕድሜ ደረጃ በላይ የሆነ ምግብ መላክ አላስፈላጊ ብክነትን ሊያስከትል ይችላል፤ ከሚያስፈልገው በታች መላክ ደግሞ ልጁ በቂ ምግብ እንዳያገኝ ሊያደርግ ይችላል። ስለዚህ፦
- የልጁን ዕድሜና የምግብ ፍላጎት መሠረት ያደረገ መጠን ማዘጋጀት።
-ልጆች በተቻለ መጠን ምግባቸውን በራሳቸው እንዲመገቡ ማስተማር።
- ምግብን እንዳያባክኑና በተገቢው ሁኔታ እንዲጠቀሙ ማስለመድ።
- ለቀኑ የሚያስፈልጋቸውን የመጠጥ ውሃ በቂ መጠን መላክ።
4. ት/ቤቱ የሚያዘጋጀውን የምግብ ዝርዝር መከተል ያለው ጠቀሜታ፡
ት/ቤቱ ለተማሪዎች የሚያዘጋጀው የምግብ ዝርዝር የዘፈቀደ ውሳኔ ሳይሆን የተማሪዎችን ጤና፣ ዕድገት፣ የምግብ ልምድና የትምህርት አካባቢ ፍላጎት ግምት ውስጥ ያስገባ እቅድ ነው።
ይህንን ዝርዝር መከተል የሚከተሉት ጠቀሜታዎች አሉት፦
1. የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ ይረዳል፦ ልጆች የተለያዩ የምግብ ዓይነቶችን በተመጣጠነ ሁኔታ እንዲያገኙ ያግዛል።
2. የምግብ ልምድን ያሻሽላል፦ ልጆች የተለያዩ ጤናማ ምግቦችን እንዲለምዱና በምግብ ምርጫቸው ላይ ጤናማ አመለካከት እንዲያዳብሩ ይረዳል።
3. የምግብ አሰራርን ሃሳብን ይቀንሳል፦ ወላጆች ት/ቤቱ በሚልከው የምግብ ዝርዝር ፕሮግራም መሠረት የተማሪዎችን ምግብ ካዘጋጁ ነገ ምን ልሰራ ከሚልዐጭንቀት ነፃ ይሆያሉ።
4. የምግብ ብክነትን ይቀንሳል፦ ወላጆች በየቀኑ የሚያስፈልገውን ምግብ በተገቢው መጠን እንዲያዘጋጁ ያግዛል።
5. የልጆችን ጤናና ደህንነት ይጠብቃል፦ የምግብ ጥራትን፣ ንጽህናንና ተገቢነትን ለመቆጣጠር ያስችላል።
6.ተማሪዎችን ከመቀናናት ስሜት ነፃ እንዲሆኑ ያደርጋል።
ስለዚህ ወላጆች ት/ቤቱ የሚያዘጋጀውን የምግብ ዝርዝር በጥንቃቄ በመከተል ከት/ቤቱ ጋር በቅንጅት መሥራት ይጠበቅባቸዋል። በልጆች የጤና ሁኔታ ወይም በምግብ ምርጫ ላይ ልዩ ፍላጎት ካለ ደግሞ ለት/ቤቱ አስቀድሞ ማሳወቅ ያስፈልጋል።
5. የወላጆችና የት/ቤት ትብብር
የልጆች ስኬት የወላጆችና የት/ቤት የጋራ ኃላፊነት ነው። ት/ቤቱ ብቻውን ወይም ወላጆች ብቻቸውን በመሥራት የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አይቻልም።
ስለዚህ ወላጆች ከመምህራንና ከት/ቤቱ አስተዳደር ጋር በቋሚነት መገናኘት፣ ስለልጆቻቸው የባህሪ፣ የጤናና የትምህርት ሁኔታ መረጃ መለዋወጥ እና በት/ቤቱ የሚዘጋጁ የወላጆች ስልጠናዎችና የግንኙነት መርሃ ግብሮች ላይ በንቃት መሳተፍ ይጠበቅባቸዋል።
6. የምስጋና መልዕክት
መርዋ ት/ቤት የልጆችን ትምህርታዊ ስኬት ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ እድገታቸውን፣ ጤናቸውን፣ ሥነ-ምግባራቸውንና የወደፊት ሕይወታቸውን በትኩረት የሚመለከት የትምህርት ተቋም ነው። ለዚህም የወላጆች ግንዛቤ ማሳደግና ከቤተሰብ ጋር ጠንካራ ትብብር መፍጠር ለት/ቤቱ ትልቅ ትኩረት ከሚሰጣቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው።
በመሆኑም በዛሬው የወላጆች ስልጠና ላይ ጊዜያቸውን ሰውታችሁ በንቃት ለተሳተፋችሁ ውድ የኬጂ ተማሪ ወላጆች ከልብ የመነጨ ምስጋናችንን እናቀርባለን።
በተጨማሪም ይህንን ጠቃሚ ስልጠና በማዘጋጀትና በማስፈጸም የደከማችሁ እና ሁሉም ወላጆች እንድሳተፉ ስልክ በመደወል ላስተባበራችሁ ውድ የወላጅ ኮሜቴዎች እንዲሁም ይህ ፕሮግራም እንዲሳካ ከፍተኛ ጥረት ላደረጋችሁ የት/ቤቱ አመራር አባላት፣ መምህራን፣ አዘጋጅ አካላትና የስልጠናውን አቅራቢዎች በሙሉ ከልብ እናመሰግናለን።
ውድ ወላጆች፣ ልጆቻችን የወደፊት ተስፋችን ናቸው። በቤት የምንሰጣቸው ፍቅርና እንክብካቤ፣ የምናስተምራቸው እሴቶች፣ የምናቀርብላቸው ጤናማ ምግብና በት/ቤት የሚያገኙት ትምህርት በአንድነት የወደፊት ማንነታቸውን ይገነባሉ።
እንግዲህ ለልጆቻችን ጤናማ አካል፣ ጠንካራ አእምሮ፣ መልካም ባህሪና ብሩህ የወደፊት ሕይወት ለመገንባት ወላጆች እና ት/ቤቶች በአንድነት እንሥራ እያልን የዕለቱም መልዕክታችንን እናጠናቅቃለን።
መርዋ ት/ቤት – የልጆች የላቀ ዕድገት፣ የወላጆች ትብብርና የማኅበረሰብ ብሩህ ተስፋ!

















