+++++++++++++++
አንቀጽ ሚዲያ መጋቢት 16/07/2018 ዓ.ም ቡኢ-ኢትዮጵያ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ አማካኝነት የተዘጋጀ ሀገር አቀፍ የአቅም ግንባታ ሥልጠና በምሥራቅ ጉራጌና ማረቆ ልዩ ወረዳ ሀገረ ስብከት በብፁዕ አባታችን አቡነ ኤጲፋንዮስ አባታዊ መመሪያ መሠረት በዛሬው እለት ተጀምሯል ።
የስልጠናው መርሐ ግብር በፀሎት ተከፍቶ የሀገረ ስብከቱ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ ክፍል ሃላፊ በሆኑት በመምህር ሲሳይ መርሐ ግብሩ የተመራ ሲሆን የምሥራቅ ጉራጌና ማረቆ ልዩ ወረዳ ሃገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ክቡር ሊቀ ካህናት ቀሲስ ሰሎሞን አባይነህ " የሚያስታርቁ ብፁዓን ናቸው የእግዚአብሔር ልጅ ይባላሉና" ማቴ 5፥9 በሚል ርዕስ ስለ ሰላም ሰፋ አድርገው ገልጸዋል።
በተጨማሪ በቅርቡ 44ኛውን ሀገር አቀፍ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ስምሪት ስልጠና መሰጠቱን በማስታወስ አገልጋዮች ዘመኑን የዋጁ ትጉህ አገልጋይ መሆን እንዳለባቸው እና በዛሬው እለት የሚሰጠውም ስልጠና ትጉህ አገልጋይ ለኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን በሚል መሪ እቅድ መሆኑን የገለፁ ሲሆን ማስታወሻ በመያዝ በንቃት መሳተፍ እንደሚገባ አሳስበዋል፤
አክለውም ክቡር ሥራ አስኪያጁ የወንጌል፣ የትህትና እና የልማት አርበኛ የሆኑትን የብፁዕ አባታችን አቡነ ኤጲፋንዮስን አባታዊ መመሪያና መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመቀጠልም "እቅበተ እምነት" በሚል ርዕስ ስልጠናው የተጀመረ ሲሆን የመጀመሪያው ክፍል ስልጠና የደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን ስብከተ ወንጌልና የመጽሐፍት መምህር በሆኑት በመጋቤ ሐዲስ ገብረ መስቀል እምነትን መጠበቅ በሚል እየተሰጠ ይገኛል
March 26, 2026 106









