ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የምሥራቅ ጉራጌና ማረቆ ልዩ ወረዳ ሀገረ… — ዜና ምስራቅ — TG.ME

ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የምሥራቅ ጉራጌና ማረቆ ልዩ ወረዳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ ቋሚ አባል በቡታጅራ ማረሚያ ተቋም ተገኝተው ታራሚዎችን ጎብኝተው የሰንጋዎች ስጦታ አበርክተዋል።

ብፁዕነታቸው በቡታጅራ ማረሚያ ሲደርሱ በካህናት አባቶች ደማቅ መንፈሳዊ  አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

የእለቱ መርሐ ግብር በብፁዕነታቸው  ጸሎትና ቡራኬ የተጀመረ ሲሆን በብፁዕነታቸው አቅጣጫ ሰጭነት የመስቃን ወረዳ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ በመጋቤ ስብሐት ቀሲስ ባዘዘው ታደሰ መርሐ ግብሩ ተመርቶ በሀገር በሽማግሌዎች የምርቃት ሥነ ሥርዓት ተከናውኗል።

በመርሐ ግብሩ ላይ ብፁዕነታቸው ባስተላለፉት አባታዊ መልዕክት የቅዱስ ዮሴፍን ታሪክ ከኦሪት ዘፍጥረት በመጥቀስ  በሕግ ጥላ ስር ለሚገኙ ታራሚዎች " እናንተ አሁን ያላችሁበት የሥጋ (የአካል እስር እንጂ የህሊና አይደለም "በማለት፣ አካል ቢታሰርም ህሊና እና መንፈስ ግን በእግዚአብሔር ቃል ነጻ ሊሆኑ እንደሚችሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ብፁዕነታቸው አያይዘውም ለታራሚዎቹ የትንሳኤ በዓል መዋያ የሚሆን የሰንጋዎች ስጦታ እንዲዘጋጅ ላስተባበሩ አካላት በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በመቀጠል በምሥራቅ ጉራጌና ማረቆ ልዩ ወረዳ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ክቡር ሊቀ ካህናት ቀሲስ ሰሎሞን አባይነህ ታስሬ መጥታችሁ ጠይቃችሁኛልና በሚል ርዕስ  መነሻ በማድረግ በመከራችን በፈተናችን የሚያረጋጋን እግዚአብሔር  መሆኑን በመጥቀስ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን ይህን በጎ አድራጎት ላስተባበሩ አካላት አመስግነዋል።

የልማትና የወንጌል አርበኛ የሆኑት ብፁዕ አባታችን  የሰንጋዎች ስጦታውን ለማረሚያ ተቋሙ ሃላፊ ኮማንደር ከድር ጀማል አስረክበዋል።

የቡታጅራ ከተማ ማረሚያ ተቋም ሃላፊ ኮማንደር ከድር ጀማል ስጦታውን በመረከብ የተሰማቸውን ትልቅ ደስታ የገለፁ ሲሆን ብፁዕነታቸውን ለታራሚዎች ላበረከቱት የትንሳኤ መዋያ የሰንጋዎች ስጦታ ላቅ ያለ ምሥጋና አቅርበዋል።

አክለውም ይህ ስጦታ በታራሚዎች ዘንድ ትልቅ ደስታ መሆኑንም ገልፀዋል ።የዞን ፍትህ መምሪያ ተወካይ ክብሩ ወልዴ ለዚህ በጎ አድራጎት የተንቀሳቀሱ አካላትን አመስግነው ትልቅ አብነት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የታራሚዎች ሊቀ መንበር ግርማ ስዩሜ እስካሁን ከተደረገልን ይህ የተደረገልን ትልቅ ነገር ነው በማለት ታራሚዎችን
በመወከል የተሰማውን ደስታና ምስጋና በመግለጽ "እስከ ዛሬ በማረሚያ ቤት በቆየሁባቸው ጊዜ ይህ የመጀመሪያ ድንቅ በጎ አድራጎት ነው" በማለት የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የምሥራቅ ጉራጌና ማረቆ ልዩ ወረዳ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ክቡር ሊቀ ካህናት ቀሲስ ሰለሞን አባይነህን ጨምሮ የመስቃን ወረዳ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ስብሐት ቀሲስ ባዘዘው ታደሰ፣ የመስቃን ወረዳ ቤተ ክህነት ሠራተኞች ፣የአድባራት አስተዳዳሪዎች ፣አባቶች ካህናትና ዲያቆናት ከፍተኛ  የመንግሥት ተወካዮችና የሀገር ሽማግሌዎች በተገኙበት መርሐ ግብሩ ተከናውኗል ።

በመጨረሻም ይህ ታላቅ መርሐ ግብር በምርቃት፣ በብፁዕነታቸው ቃለ ምዕዳንና አባታዊ ቡራኬ በሰላም ተጠናቋል።  
                        አንቀጽ ሚዲያ
የምሥራቅ ጉራጌና የማረቆ ልዩ ወረዳ ሀገረ ስብከት
        ለቤተክርስቲያን አገልግሎት እንተጋለን !!!
             መጋቢት 22/07/2018 ዓ.ም
                       ቡኢ-ኢትዮጵያ
March 31, 2026 131