#የሰራተኞችድምጽ🔈 የላብ አደሩ ቀንና በበዓል ድምቀት የማይሸፈነው የኑሮ ፈተና ! (የሰራተኞች ድምጽ - በቲክቫህ ኢትዮጵያ) ዛሬ ሚያዝያ 23 የዓለም የላብ አደሮች ቀን ነው። ይህ ቀን ለብዙዎች የእረፍት እና የደስታ ሊሆን ቢችልም ለብዙሃኑ ሰራተኞች ግን የድካማቸው ውጤት ከኑሮ ጋር ግብግብ የሚገጥሙበትን እውነት የሚያስታውስ ነው። በየኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ፣ በፋብሪካዎች ፣ በግንባታ ቦታዎች እና በተለያዩ ተቋማት ውስጥ ቀን ከሌሊት የሚደክመው ሰራተኛ ዛሬም ድረስ በበርካታ ማነቆዎች ውስጥ ይገኛል። ዛሬ ሰራተኛው እየተጋፈጠ ያለው ትልቁ ፈተና የኑሮ ውድነት ነው። ከቤት ኪራይ ጭማሪ እስከ ትራንስፖርት ጣጣ፣ ከምግብ ዋጋ መናር እስከ መሰረታዊ ፍላጎቶች አለመሟላት ሰራተኛውን ለከፍተኛ የስነ-ልቦና እና የኢኮኖሚ ጫና ዳርገውታል። የሚያገኘው ደመወዝ በወሩ መጀመሪያ ላይ " እጁ ገብቶ ሳይታይ " የሚያልቅበት ደረጃ ላይ ደርሷል። በሀገራችን እስካሁን የዝቅተኛ ደመወዝ ወለል አለመወሰኑ ለብዙዎች ብዝበዛ ምክንያት እንደሆነ ሰራተኛው ይገልጻል። በተለይም በኢንዱስትሪ ፓርኮች እና በተለያዩ የግል ድርጅቶች ውስጥ የሚሰሩ ወገኖቻችን በወር የሚያገኙት ገቢ ከእለታዊ ፍጆታቸው ጋር በፍጹም የማይመጣጠን ነው። የላባቸውን ዋጋ፤ የድካማቸውን በረከት ማግኘት አልቻሉም። የሚገርመው ደግሞ ሰራተኛው መብቱን ሲጠይቅ ወይም የተሻለ ክፍያ ሲፈልግ " ምንም አታመጡም፤ ካልፈለጋችሁ መልቀቅ ትችላላችሁ " የሚል የማስፈራሪያ ቃል መጋፈጡ ነው። ስራ አጥነትን እንደ ማስፈራሪያ በመጠቀም የሰራተኛውን ክብር እና መብት የሚጥሱ አካላት ዛሬም አልጠፉም። የሰራተኛ ማህበራት ጥንካሬ ማጣትም ለዚህ ክፍተት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል። በርካታ ድርጅቶች በየዓመቱ በሚሊዮን እና በቢሊዮን የሚቆጠር ትርፍ ሲያሳውቁ ይሰማሉ። ነገር ግን ይህ ትርፍ እንዲመጣ ዋናው ሞተር የሆነው ሰራተኛ ህይወቱ ላይ ምንም ለውጥ አይታይም። " ድርጅታችን አደገ " ሲባል የሰራተኛው ኑሮ ግን አብሮ ካላደገ እድገቱ ትርጉም አልባ ነው። ሰራተኛው የድርጅቱ አካል ፣ ምሰሶ የጀርባ አጥንት መሆኑን መዋጥ የግድ ነው። የላብ አደሮች ቀን በባዶ ቃላትና በንግግር ብቻ የሚታለፍ መሆን የለበትም። የሰራተኛውን ኑሮ ለማሻሻል የሚያስችሉ ተጨባጭ የፖሊሲ ማሻሻያዎች፣ የደመወዝ ወለል መወሰን እና የመብት ጥበቃዎች ሊተገበሩ ይገባል። ላቡን አፍስሶ ሀገር ለሚገነባው፣ ደሙን አፍስሶ ለሚያመርተው ሰራተኛ ሁሉ ክብር ይገባዋል! መልካም የላብ አደሮች ቀን! ቲክቫህ ኢትዮጵያ ሚያዚያ 23 ቀን 2018 ዓ/ም @tikvahethiopia
Major Crypto Airdrops: post #2401 — TG.ME
May 1, 2026 26