ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካ የሚኖሩ ስደተኞች ከመንግስት የሚያገኙትን የዕርዳታ ድጋፍ (Welfare) የሚያሳይ ዝርዝር መረጃ በሰንጠረዥ መልክ በትሩዝ ሶሻል አካውንታቸው ላይ አጋርተዋል።
ፕሬዝዳንቱ በማህበራዊ ገፃቸው ባጋሩት መረጃ መሰረት፣ በአሜሪካ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ተወላጅ ቤተሰቦች ከሌሎች ሀገራት አንጻር ከፍተኛ የሚባል የመንግስት ድጋፍ ተጠቃሚ መሆናቸውን ያሳያል።
መረጃው በአሜሪካ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ተወላጅ ስደተኛ ቤተሰቦች (Immigrant Households) 47.6 በመቶ ያህሉ ቢያንስ ከቤተሰቡ አንዱ የመንግስት ማህበራዊ ድጋፍ ተጠቃሚ መሆናቸውን የሚገልጽ ነው።
ምንም እንኳን ቤተሰቦቻቸው ሰራተኛ ቢሆኑም አሜሪካ ውስጥ የተወለዱ ልጆቻቸው በመንግስት በሚደገፍ የነጻ የትምህርት ቤት ምሳ ወይም የጤና መድን ተጠቃሚ ከሆኑ፣ ያ ሙሉ ቤተሰብ እንደ "ዕርዳታ ተቀባይ" ተቆጥሮ በዝርዝሩ ውስጥ መካተቱ ቁጥሩን ከፍ አድርጎታል።
ይህ የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ መረጃ በኢትዮጵያውያን ላይ ከስነ-ልቦና ጫና ባለፈ፣ ወደፊት የሚደረጉ የቤተሰብ ጥሪዎችንና የቪዛ ሂደቶችን አደጋ ላይ የሚጥል እንደሆነ ይታመናል።
ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉትና በአሜሪካ የህግ ባለሞያ የሆኑት አቶ ሙሉአለም ጌታቸው በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጹሑፍ "በዚህ መጠን የኢትዮጵያ ስደተኛ በዌልፌር ሥር መሆኑ አስደሳች ዜና አይደለም" ሲሉ ገልጸውታል።
አክለውም፥ " ይሄ ከኢትዮጵያ ለሚመጣ ስደተኞች መጥፎ የፖሊሲ አቅጣጫ ሊያስቀምጥ ያችላል። አሁን ትኩረቱ እኛ ላይ ላይሆን ይችላል። ነገር ግን የምትችሉ ሰዎች ከዌልፌር መውጣት ብትችሉ የተመረጠ ነው።" የሚል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
| @tikvahethmagazine

