በስመ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ዛሬ ጳጒሜን 2 ❤ እንኳን ከሰባ_ሁለቱ_አርድእት… — ኩራዝ — TG.ME

"በስመ አብ ወወልደ  ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"።                 ዛሬ ጳጒሜን 2 ❤ እንኳን ከሰባ_ሁለቱ_አርድእት አንዱ ለሆነው ሐዋርያው #ቅዱስ_ጳውሎስ_መልእክት_ለጻፈለት ለከበረ #ለሐዋርያው_ለቅዱስ_ቲቶ ለዕረፍት በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።                           ✝ ✝ ✝ ❤ #ሐዋርያው_ቅዱስ_ቲቶ፦ የዚህም ቅዱስ ትውልዱ ቀርጤስ ከሚባል አገር ነው። እርሱም ለዮናናውያን ወገን ለሆነ ለአገረ ገዥው እኅት ልጅዋ ነው። ከታናሽነቱም የዮናናውያንን ትምህርትና ፍልስፍና ተምሮ እጅግ አዋቂ ሆነ በጠባዩም ቅን ሥራው ያማረ ለድኆችና ለችግረኞች መራራት የሚወድ ነው። ከሌሊቶችም በአንዲቱ "ቲቶ ሆይ ስለ ነፍስህ ድህነት ተጋደል ይህ ዓለም አይጠቅምህምና" የሚለውን በሕልሙ አየ። ከእንቅልፉም በነቃ ጊዜ ደነገጠ ምን እንደሚሠራም አላወቀም። ❤ ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት በተሰማ ጊዜ ብዙዎች ሰዎችም ተአምራቱን እርስበርሳቸው ተነጋገሩ የአክራጥስ መኰንንም ሰምቶ አደነቀ ዕውነት እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ ወይም የሥራይ እንደሆነ ሊያውቅ ሽቶ የሚልከው ብልህ ሰው ፈለገ የእኅቱንም ልጅ ቲቶንን መረጠው ከእርሱ የሚሻል የለምና። ሲልከውም ታላቅና ጥልቅ የሆነ ምርመራ እንዲመረምር አዘዘው። ❤ ቲቶም ከይሁዳ ምድር በደረሰ ጊዜ የመድኃኒታችንን ድንቆች የሆኑ ተአምራቶቹን አየ ሕይወትነት ያላቸው ትምህርቶቹንም ሰማ። ከዮናናውያንም በትምህርታቸውና በሥራቸው መካከል ታላቅ የሆነ መራራቅን አግኝቶ የዮናናውያን ሃይማኖታቸው የቀናች እንዳልሆነች ለይቶ ዐወቀ። ❤ ከዚህም በኋላ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ አመነ፤ ደቀ መዝሙሩም ሁኖ ተከተለው። ወደ እናቱ ወንድም ወደ አገረ ገዥውም መልእክትን ላከ የክብር ባለቤት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚያስተምረውና የሚሠራው ዕውነት እንደሆነ ነገረው። ❤ ጌታችንም ከሰባ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ውስጥ የተቆጠረ አደረገው ከዕርገቱም በኋላ ከሐዋርያት ጋር የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ተቀብሎ ከእሳቸው ጋር በሀገሮች ሁሉ ዙሮ አስተማረ። ጌታችንም ጳውሎስን ጠርቶ ሐዋርያው በአደረገው ጊዜ ያን ጊዜ ሐዋርያ ጳውሎስን ተከተለው በብዙ አገሮችም ወንጌልን ሰበከ። የከበረ ቅዱስ ጳውሎስም በሮሜ ከተማ ምስክር ሆኖ ከሞተ በኋላ ቅዱስ ቲቶ ወደ ሀገረ አክራጥስ ተመለሰ ቤተ ክርስቲያንም ሠርቶ ቀሳውስትንና ዲያቆናትን ሾመላቸው በዙሪያቸው ላሉ አገሮችም እንዲሁ አደረገ። ❤ ከዚህም በኋላ ሐዋርያዊ አገልግሎቱን ፈጽሞ ወደ ወደደው እግዚአብሔር ጳጒሜን 2 ቀን ሔደ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በሐዋርያው ቅዱስ ቲቶ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።                                              ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "ቀዳሚሃ ለጥበብ ፈሪሃ እግዚአብሔር። ምክር ሠናይት ለኵሉ ዘይገብራ። ወስብሐቲሁኒ ይነብር ለዓለም"። መዝ 110፥10። የሚነበቡት መልዕክታት ቲቶ 1፥1-11፣ 2ኛ ጴጥ 3፥7-14 እና የሐዋ ሥራ 4፥31-36። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 10፥1-12። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱሳን ሐዋርያት ቅዳሴ ነው። መልካም የሐዋርያው የቅዱስ ቲቶ የዕረፍት በዓልና የጾም፣ የጸሎትና የምሕላ ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።አሜን                    

September 7, 2026 227