🌿 “አልጋችንም ለምለም ነው”
እህቶች ሆይ ሰውነታችን ምን ያህል የተቀደሰ እንደሆነ እንመለከት ዘንድ ወደ መኃልየ መኃልይ ጎራ ብለን ይህቺን ኃይለ ቃል እንመርምራት። “አልጋችንም ለምለም ነው” መኃ 1÷7 የመጀመሪያው ቃል አልጋችን የሚለው ነው። በመኃልይ ውስጥ ያለችው ሙሽራ ሰውነቷ የራሷ ብቻ ሳይሆን የሙሽራዋም እንደሆነ ትናገራለች።ሰውነታችን በመንፈሳዊ መንገዳችን ላይ እየገባ ከጽድቅ የሚያደናቅፈን አይደለም።ይህ የግኖስቲኮች አስተምህሮ ነው። በክርስትና ይህን አንማርም ቤተክርስቲያን “ነፍስ ጥሩ ናት ሥጋ ግን ክፉ ነው” አትልም። ሥጋችንም እንኳ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ቤተመቅደስ ይሆን ዘንድ እንደተጠራ ታምናለች። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ሥጋችሁ የክርስቶስ ብልቶች እንደ ሆነ አታውቁምን? እንግዲህ የክርስቶስን ብልቶች ወስጄ የጋለሞታ ብልቶች ላድርጋቸውን? አይገባም።” 1ቆሮ 6÷15 በማለት ሰውነታችን የከበረ እና ከእግዚአብሔር ጋር በሚኖረን አንድነት ውስጥም የሚሳተፍና የሚተባበር መሆኑን ይነግረናል።በነፍሳችን ውስጥ የሚፈጠር ማናቸውም ነገር ከጊዜ ብዛት ሰውነታችንን በምንጠቀምበት መንገድ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። ክርስቶስ ወደ ልባችን ከገባ ልባችን ይለወጣል ሰውነታችንም ቅዱስ የሆነውን ነገር መሥራት ማገልገል ይጀምራል።ንጽሕና፣ ደግነት፣ ራስን መግዛት፣ ሌሎችን ማገልገል እነዚህ ሁሉ በሰውነት ላይ ይገለጣሉ።
ወደ ሙሽሪት እንመለስና ቃሏን እንመርምር “አልጋችን ለምለም ነው” አለች የለመለመ ነው የሚለው ቃል ፍሬያማነትን የሚያመለክት ነው።አስቀድሞ ለኃጢአት እንጠቀመው የነበረ ሰውነት በእግዚአብሔር ከኖረ ፍሬያማ መሆን ይችላል። ዘውትር እየሰራን መላቀቅ ያቃተን ኃጢአት ካለ ኃጢአቱን በሰራን ጊዜ መጠየቅ ያለብን ጥያቄ ሰውነቴን መጥፎ ነገርን ከመስራት እንዴት ልግታው? የሚለው ሳይሆን ሰውነቴ በክርስቶስ ሕይወት ፍሬ የሚያፈራበት ቅርንጫፍ እንዴት ላድርገው? ብለን ነው።በዚያን ጊዜ አይኖቻችን በፍቅር ይመለከታሉ።አንደበታችን ከሐሜት ይልቅ በረከትን ምርቃትን ያወጣል፣ እጆቻችን ሌሎችን ለማገልገል ይተጋሉ፣ ሰውነታችን በጎነትንና ራስን መግዛትን ይለማመዳል። እናም ሙሽሪት የጠቀሰችው ያ ለምለም አልጋ ኃጢአት የማይሰራ ሰውነት ብቻ ሳይሆን በክርስቶስ የሚያፈራ ሰውነት ነው።አባ ታድሮስ ማላቲ ይህንኑ የመኃልይ ክፍል ማብራሪያ በሰሩበት መጽሐፋቸው ይህ መኝታ የክርስቶስን ሥጋዌ የሚያመለክት እንደሆነ ይነግሩናል።ይህም ጥቅሱን ይበልጥ ጥልቅ መልዕክት እንዳለው የሚያስረዳን ነው።ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የኛን ሥጋ ነሳ የእርሱ አካል አልታዘዝ ባልንበት ቦታ ሁሉ የታዘዘ፣ ባደፍንበት ቦታ ሁሉ ንጹሕ የሆነ፣ በተሸነፍንበት ቦታ ሁሉ ድልን የተቀዳጀ ነበረ። እኛም ራሳችንን ከእርሱ ጋር ለማዋሐድ በፈቀድን ጊዜ የሚፈጠረው ይሄ ነው የእርሱ ሰው መሆን መዳናችን የተቀዳበት ምንጭ ነው።እርሱም ሰው ሆኖ የኛን ባሕርይ በመንሳት ከእግዚአብሔር ጋር አንድ ወደመሆን ከፍ ያደረገው ነው።ለዚህም ነው ይህ መኝታ “አልጋችን” ተብሎ የሚጠራው።አንድነት አለ።የእርሱ ከሆነው መሳተፍ የምንችል እንሆን ዘንድ እርሱ የእኛ የሆነውን ነሳ።እናም እህቶች ሆይ ክርስቶስ እንደሚወደን እንደሚለውጠን፣ እኛም ክርስቶስን በማየት ከእርሱ ጋር አንድ በመሆን በእርሱ ፍሬ እናፈራ ዘንድ ሰውነታችንን ከዚህ ዓለም ከንቱ ምኞት እንጠብቅ።








