የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ከታዋቂው ማሪዮት ኢንተርናሽናል ጋር በመተባበር የሚያካሂደው ይህ ግንባታ፣ ነባሩን እና ታሪካዊውን ጣና ሆቴል ወደ ዓለም አቀፍ ደረጃ በማሸጋገር የከተማዋን ገጽታ ሙሉ በሙሉ የሚቀይር ይሆናል።
የፕሮጀክቱ ንድፍ በዚያስ (ZIAS) አርክቴክቸር የተሰራ ሲሆን፣ የእይታ ሞዴሉ ደግሞ በቤቶን ሞዴል ሰሪዎች በጥራት ተዘጋጅቷል።
በሶስት ቢሊዮን ሶስት መቶ ሚሊዮን ብር ወይም በአሜሪካን ዶላር ሲሰላ 20 ነጥብ 9 ሚሊዮን በሚጠጋ በጀት የሚገነባው ይህ ዘመናዊ ፎር ፖይንትስ ባይ ሼራተን ሆቴል፣ 32 ሺህ 440 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ነው። ሆቴሉ ግንባታው ተጠናቆ በኖቬምበር 2027 እ.ኤ.አ. ለአገልግሎት ሲበቃ፣ 120 ዘመናዊ የእንግዳ ማረፊያ ክፍሎችን፣ አራት የተለያዩ የምግብ አዳራሾችን፣ የላቀ እስፓ እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዕከል፣ የመዋኛ ገንዳ እና መዝናኛዎችን አካቶ ይይዛል።
በተጨማሪም ከ1 ሺህ በላይ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል ትልቅ የጉባኤ አዳራሽ የሚኖረው ሲሆን፣ ይህም ለሀገር ውስጥ እና ለዓለም አቀፍ ስብሰባዎች፣ ለንግድም ሆነ ለመዝናናት ለሚመጡ እንግዶች ምቹ ከባቢን ይፈጥራል።
ይህ ፕሮጀክት በጣና ሐይቅ ዙሪያ ያለውን የሆቴል አገልግሎት ጥራት ከፍ የሚያደርግ ሲሆን፣ ባህር ዳርን በኢትዮጵያ ቀዳሚ የቱሪዝም እና የስብሰባ ማዕከል አድርጎ ለማስቀጠል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል።



















