Holy Trinity Elementary ,2016: post #4869 — TG.ME

Forwarded fromARArada subcity communication

ዋጋው ከ70,000 ብር በላይ የሆነውን ስልክ ወድቆ ያገኘውና ለባለቤቱ ያስረከበው ሹፌር ጅላሉ አራዳ ሀምሌ 28/2018 ዓ.ም የአራዳ ክ/ከተማ አስተዳደር ሰራተኛ ጅላሎ ያሲን የክ/ከተማ አስተዳደሩ ምክትል ስራ አስፈጻሚ ሹፌር በመሆን ያገለግላል ። ለአራዳ ክ/ከተማ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት በሰጠው አስተያየት ታማኝነት የኢትዮጵያውያን ባህል መገለጫ መሆኑን ገልፆ የሰውን ገንዘብ ለግል ጥቅም ማዋል በሰውም ሆነ በፈጣሪ ፊት የሚያስነቅፍና የሚያሳፍር ተግባር መሆኑን ተናግሯል ። ከ70,000 ብር በላይ ዋጋ ያለውን ስልክ ማን እንደጣለውና እንዴት እንዳገኘው ሲያብራራ በአራዳ ክ/ከተማ አስተዳደር ግቢ ውስጥ ከሚገኘው የመኪና ማቆሚያ ቦታ ላይ ከአንድ መኪና ስር የወደቀ ስልክ ማየቱንና አንስቶ የስልኩን ባለቤት ለማወቅ ፍላጎት እንዳደረበት ገልፆ ስልኩ ውድ ስልክ እንደሆነ አውቃለሁ፤ ከአስተዳደጌም ሆነ አብሬያቸው ከምሰራው ሀላፊዎች የተማርኩት ታማኝነትን፣ የስራ ትጋትን፣ የሰውን ሀቅ ለግል ጥቅም አለማዋልን በመሆኑ ያገኘሁትን ስልክ ለመውሰድ ምንም አይነት ፍላጎት አላደረብኝም ያለ ሲሆን ስልኩን እንዳገኘሁት ለስራ ከግቢው ወጥቼ የነበረ ቢሆንም ሊፈልጉ እንደሚመጡ ስለተረዳሁ በፍጥነት ወደግቢው ተመለስኩ ሲል ገልጿል ። እንደተመለስኩም ባለቤቱን በማግኘቴ ስልኩን አስረክቤያለሁ ብሏል። ስልኩ ከጠፋብኝ በላይ ያስገረመኝ መመለሱ ነው ያለው የስልኩ ባለቤት አቶ ጌታነህ ለገሰ ከስልኩ ይልቅ በውስጡ የነበረውን መረጃ ማጣቱ ሲያሳስበው እንደነበር አልሸሸገም። እንደዚህ ያሉ ሰዎች ይኖራሉ ብዬ አላምንም ነበር ያለው አቶ ጌታነህ ለሰዎች ያለኝን ግምት እንድቀይርና በጎነትን እንድማር አድርጎኛል ያለ ሲሆን የሹፌር ጅላሎን ምግባር ሁላችንም ልንጋራ ይገባል ሲል ምስክርነቱን ሰጥቷል።

August 5, 2026 2.3K