በአዲስ አበባ-ወልቂጤ መስመር ከባድ ዝርፊያ የፈጸሙ አካላት በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ
ወልቂጤ | ዘቢዳር ሚዲያ (ሐምሌ 24 ቀን 2018)
ከአዲስ አበባ ወደ ወልቂጤ በመጓዝ ላይ በነበረ የተሽከርካሪ እና ጭነት ላይ ሐምሌ 23 ቀን 2018 ከባድ የዝርፊያ ወንጀል የፈጸሙ ተጠራጣሪዎች በፖሊስ እና በጸጥታ አካላት በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ።
እንደቀረቡት መረጃዎች ገለጻ የሰሌዳ ቁጥሩ ማ/ኢ ኮድ 3 - 03175 የሆነ አይሱዙ ተሽከርካሪ ከኦሮሚያ ጎሮ ወረዳ ወደ ፌንጭር በሚወስደው መንገድ ላይ በመጓዝ ላይ እያለ የፖሊስ የደንብ ልብስ (Uniform) የለበሱና ታጣቂ የሆኑ አካላት ተሽከርካሪውን አስቁመዋል። ተጠራጣሪዎቹ አሽከርካሪውን እና ረዳቱን በጫካ ውስጥ በገመድ ካሰሩ በኋላ ተሽከርካሪውን ይዘው ለመሰወር ሙከራ ማድረጋቸው ተመልክቷል።
በወቅቱ ተሽከርካሪው ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ የዋጋ ግምት ያላቸው ልዩ ልዩ ውድ ዕቃዎችን ጭኖ የነበረ ሲሆን ዘራፊዎቹ የተጫኑትን ዕቃዎች በከፊል በቀቤና ልዩ ወረዳ ወሸርቤ በኩል ካራገፉ በኋላ የቀሩትን ይዘው ወደ ወልቂጤ ከተማ ሲገቡ መያዛቸው ተገልጻል።
የጎሮ ወረዳ ፖሊስ፣ የወልቂጤ ከተማ ፖሊስ እና የጸጥታ የጋራ ግብረ-ኃይል ከህብረተሰብ በተገኘ መረጃ መሰረት ባደረጉት ከፍተኛ ክትትል ተሽከርካሪውን እና ተጠርጣሪዎቹን ከነታጠቁት ትጥቅ በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል። ከተያዙት ተጠራጣሪዎች መካከል አንደኛው አብዲ መኪ (በቅጽል ስሙ "ስሪሲክስ") የተባለ አሽከርካሪ እንደሚገኝበት ተጠቅሷል።
በጉራጌ ዞን እና በወልቂጤ ዙሪያ ባሉ አካባቢዎች በተለያዩ ጊዜያት የሚፈጸሙ የዝርፊያና የጸጥታ መዛባት ድርጊቶች የዜጎችን የመንቀሳቀስና የንግድ እንቅስቃሴ አደጋ ላይ እየጣሉ መሆኑን ነዋሪዎች ይናገራሉ። ህብረተሰቡ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ እና መሰል ህገ-ወጥ ድርጊቶችን የሚፈጽሙ አካላት ላይ የሚመለከታቸው የጸጥታ አካላት የማጋለጥ ህጋዊ እርምጃ እንዲወስዱ አጥብቀው ጠይቀዋል።
በተጨማሪም ወንጀለኞችን አሳልፈው በመስጠትና በቁጥጥር ስር እንዲውሉ በማድረግ ረገድ ድጋፍ ላደረጉ ህብረተሰቦች እና የጸጥታ አካላት ምስጋና የቀረበ ሲሆን፣ መሰል የቅንጅት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ የቀረበ ሲሆን፣ ዘቢዳር ሚዲያ ጉዳዩን አስመልክቶ ከዞኑና ከተማው ፖሊስ መምሪያ ተጨማሪ ይፋዊ መግለጫዎችን በመከታተል ለተከታታዮቿ የምታደርስ ይሆናል።
ዘቢዳር ሚዲያ፦ እውነትን ለትውልድ!
#SecurityNews #Wolkite #GurageZone #CrimeReport #ZebidarMedia #ወልቂጤ #የጸጥታ_ዜና #ወንጀል #ዘቢዳር_ሚዲያ #ህግ_ማስከበር














