#ከተራራው ግርጌ
ከቅዱሱ ተራራ ግርጌ ዘጠኙ ደቀ መዛሙርት ተቀምጠዋል፡፡ ነቢዩ “አቤቱ በድንኳንህ ውስጥ ማን ያድራል? በተቀደሰውስ ተራራህ ማን ይኖራል” / መዝ.14፥1/ በማለት ጠይቆ ወደ ተቀደሰው ተራራ የሚወጡ ሰዎች ምን ዓይነት ሕይወት ያላቸው ሊሆን እንደሚገባ ሲገልጥ “… በአንደበቱ የማይሸነግል፤ በባልንጀራው ላይ ክፉትን የማያደርግ … በንፁሑ ላይ መማለጃን የማይቀበል ….” በማለት የጠቀሳቸው ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ /መዝ. 14፥1-5/ ወደ ቅድስናው ስፍራ ወጥቶ ምስጢር ለማየት ብቃት ያልነበረው ይሁዳን ለመለየት አምላክ ባወቀ ዘጠኙን ከተራራው ግርጌ አቆይቷቸዋል፡፡
“የኃጥእ ዳፋ ጻድቁን ያዳፋ” የሚል ብሂል አለ፡፡ ይህ አባባል ግን ከተራራዉ ግርጌ ለቀሩት ደቀ መዛሙርት አይሆንም፡፡ ይሁዳን በጥበብ ከምስጢር ለየው እንጂ ጌታ ስምንቱ ደቀ መዛሙርቱን የምስጢሩ ተካፋይ አድርጓቸዋል፡፡ ለጥፋቱ ምክንያት እንዳያገኝ ከምስጢሩ ቢለየኝ ከሞቱ ገባሁበት እንዳይል በጥበብ ይህን አደረገ፡፡ ስምንቱ ደቀ መዛሙርት ግን በንጹሕ ልቡና ከተራራው ግርጌ ተቀምጠውም ምስጢር አልተከለከላቸውም፡፡ ምክንያቱም “ልበ ንጹሐን ብፁዓን ናቸው እግዚአብሔርን ያዩታልና” /ማቴ.5/፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያ እግዚአብሔርን ለማየት ለሚወዱ “ትቀደሱም ዘንድ ፈልጉ ያለ እርሱ ጌታን ሊያይ የሚቻለው የለምና” እንዲል፡፡ /ዕብ.11/፡፡
#ሙሴና ኤልያስ ለምን ተመረጡ?
ሙሴንና ኤልያስን ወደ ደብረ ታቦር እንዲመጡ ያደረገበት ምክንያት የባሕርይ አምላክ መሆኑን እንዲመሰክሩ ነው፡፡ ሙሴን ከመቃብር ተነሥቶ ስለጌታችን እንዲህ የሚል ምስክርነት ሰጥቷል፡- “እኔ ባሕር ብከፍልም፤ ጠላት ብገድልም፤ ደመና ብጋርድም፤ መና ባወርድም እስራኤልን ከክፋታቸው መልሼ ማዳን ያልተቻለኝ ደካማ ነኝ፤ የእኔን ፈጣሪ እንዴት ሙሴ ይሉሃል? የሙሴ ፈጣሪ እግዚአብሔር ይበሉህ እንጂ!” ኤልያስም ደግሞ ከብሔረ ሕያዋን መጥቶ “እኔ ሰማይ ዝናብ እንዳይሰጥ ብለጉም፣ እሳት ባዘንብም፣ እስራኤልን ከክፋታቸው ማዳን የማይቻለን ነኝ እንዴት የእኔን ፈጣሪ ኤልያስ ነህ ይሉሃል? የኤልያስ ፈጣሪ እግዚአብሔር ይበሉህ እንጂ!” ብለው የባሕርይ አምላክነቱን በደብረ ታቦር ላይ መስክረዋል፡፡ በማቴ.16፡14 ላይ “አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ አሉት።” ይላልና፡፡
ሙሴና ኤልያስ የተመረጡበት ሌላው ምክንያት ሙሴ “ጀርባዬንም ታያለህ፤ ፊቴ ግን አይታይም” ተብሎ ስለተነገረለት /ዘጸ.33፡23/ ኤልያስ “በኋለኛው ዘመን ምስክሬ ትሆናለህ” ስለተባለ ያንን ለመፈጸም ነው፤ ካገቡት ሙሴን ከደናግል ኤልያስ ያመጣቸው መንግሥተ ሰማያት በሕግ የተጋቡ ሕጋውያንና ሥርዐት ጠብቀው የሚኖሩ ደናግላን እንደሚወርሷት ለማስተማር ሁለቱን መርጧቸዋል፡፡
6
2August 18, 2026 1.3K 10