ፈለገ ጥበብ ሚዲያ felegetbeb media: post #16152 — TG.ME

የ2018 ዓ.ም የሀገረ ስብከት አቀፍ ምዘና በምስራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት በቢሾፍቱ ከተማና አካባቢዎች ሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት በተሳካ ሁኔታ ተከናወነ

"እግዚአብሔር የሥራችሁንና ስለ ስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር አይረሳም።" (ዕብራውያን ፮፥፲)

የ2018 ዓ.ም የሀገረ ስብከት አቀፍ የ4ኛና 8ኛ ክፍል የሰንበት ትምህርት ቤቶች ምዘና ዛሬ ሀምሌ 26 ቀን 2018 ዓ.ም. ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ጀምሮ በምስራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት በቢሾፍቱ ከተማና አካባቢዎች ሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት በተሳካ ሁኔታ ተካሂዷል። በዚህም ምዘና ከ600 በላይ ተማሪዎች በሥነ ሥርዓትና በሰላም ተሳትፈው ፈተናቸውን ወስደዋል።
በመላው ሀገራችን በተካሄደው በዚህ ታላቅ መንፈሳዊ አገልግሎት ፈተናው በሰላምና በተሳካ ሁኔታ እንዲፈጸም በቸርነቱ ለረዳን ልዑል እግዚአብሔርን በመጀመሪያ ምስጋና፣ ክብርና ምስጋና ለዘላለሙ እናቀርባለን።
በተጨማሪም ይህ ታላቅ አገልግሎት በተሳካ ሁኔታ እንዲፈጸም በጸሎት፣ በጊዜ፣ በጉልበት፣ በምክር፣ በሐሳብና በተግባር ከጎናችን ለቆማችሁ ሁሉ ከልብ የመነጨ ምስጋናችንን እናቀርባለን።
በተለይም፦
ለምስራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ሥራ አመራሮች፤
ለቢሾፍቱ ከተማና አካባቢዎች የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ሥራ አመራሮች፤
ለሁሉም የሰንበት ትምህርት ቤቶች ሥራ አመራሮች፣ መምህራን፣ አባላትና ወላጆች፤
እንዲሁም ለቢሾፍቱ ማዕከል ማህበረ ቅዱሳን፤
በዚህ ክቡር አገልግሎት ላይ ላበረከታችሁት ከፍተኛና የማይተካ አስተዋጽኦ በእግዚአብሔርና በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስም ከልብ እናመሰግናለን።
የምታከናውኑት አገልግሎት የዛሬን ፈተና በማስፈጸም ብቻ የሚገደብ ሳይሆን፣ የነገውን የቤተ ክርስቲያንና የሀገር ተረካቢ ትውልድ በእምነት፣ በዕውቀት፣ በሥነ ምግባርና በአገልግሎት መንፈስ የማነጽ ቅዱስ ተልዕኮ ነው። ይህም በእግዚአብሔር ፊት ታላቅ ዋጋና ክብር ያለው አገልግሎት ነው።
ልዑል እግዚአብሔር የእያንዳንዳችሁን ድካም በበረከት ይተካ፤ አገልግሎታችሁን ያሳድግ፤ አንድነታችሁን ያጽና፤ በመንፈሳዊ ጥበብና በጸጋ ያበልጽጋችሁ፤ በቅድስት ቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ የምታበሩትን የእምነት ብርሃን ይበልጥ ያብራ።


የቢሾፍቱ ከተማና አካባቢዎች የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት
ጽ/ቤት

#ፈለገ_ጥበብ_ሚዲያ
#FTM
❤4