በቃሉ የፀና፣ ለሀገር የቆመ ጀግና ሠራዊት የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ጷጉሜ 02 ቀን 2018 ዓ.ም የኢትዮጵያ… — FDRE Defense Force - የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት — TG.ME

   በቃሉ የፀና፣ ለሀገር የቆመ ጀግና ሠራዊት

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ጷጉሜ 02 ቀን 2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከኢትዮጵያ ሕዝቦች አብራክ የተገኘ፣ ከህዝብ ማህፀን ምድር የተወለደ፣ የሀገርን ክብር፣ ሉዓላዊነትና ነፃነት ከልቡ የሚያከብር ጀግና  ሠራዊት ነው። የአባቶቹን የጀግንነት ታሪክ በትከሻው ተሸክሞ፣ የትናንቱን ክብር ወደ ዛሬ እና የዛሬውን አደራ ወደ ነገ እያስተላለፈ የሚጓዝ አኩሪና ባለድል ሠራዊትም ነው።

በየዘመናቱ ኢትዮጵያን በጽናት የጠበቀ፣ በፈተና ጊዜ ያልተናወጠ፣ በችግር ፊት ያልተሸማቀቀ፣ የተሰጠውን ተልዕኮና ግዳጅ በብቃት፣ በዲሲፕሊንና በጀግንነት የፈጸመ ነው ጀግናው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት

ጽናት ማለት አለመውደቅ ብቻ አይደለም፤ ቢወድቁም ተነስቶ መቀጠል ነው። ጽናት ማለት ቃል መግባት ብቻ አይደለም፤ ቃሉን በተግባር ማረጋገጥ ነው።
ጽናት ማለት ስለሀገር ፍቅር መናገርም ብቻ አይደለም፤ ለሀገር በተግባር መቆም ነው።

የሠራዊታችን ጽናት በዚህ እምነት ይገለጻል። በቃሉ ይታመናል፤ በግዳጁ ይፀናል፤ በአደራው ይታመናል። ለሀገር ሲል የሚከፍለው መስዋዕትነት፣ ለሕዝብ ሲል የሚያደርገው ተጋድሎ እና በፈተና ውስጥ የሚያሳየው ጽናት የሀገር አደራን በተግባር የሚያረጋግጥ ምስክር ነው።

የጽናት ቀን የሠራዊታችንን የተጋድሎ ታሪክ የምናስታውስበት ብቻ አይደለም። ለሀገር ሲሉ ሕይወታቸውን ለሰጡ ጀግኖች ክብር የምንሰጥበት፣ የተረከብነውን የሀገር አደራ የምናስብበት፣ የዛሬውን ሠራዊት ብርታት እና የነገዋን ኢትዮጵያ የምናስብበት የኩራት፣ የማስታወሻ እና የአደራ ቀን ነው።

ሠራዊታችን ለኢትዮጵያ ሲል በጽናት ታግሏል፤ ለሕዝቦቻችን ሰላምና ደህንነት ሲል የሕይወት መስዋዕትነት ከፍሏል። የወደቁት ጀግኖች በሰጡት ሕይወት፣ የቆሙት ጀግኖች በያዙት ቃል እና የሚመጣው ትውልድ በሚረከበው አደራ መካከል የማይቋረጥ የሀገር ታሪክ ተጽፏል።

የሠራዊታችን ጽናት በጦር ሜዳ ብቻ የሚመዘን አይደለም። ሀገርን በሰላም ማስቀጠል፣ የሕዝብን ደህንነት መጠበቅ፣ ሉዓላዊነትን ማስከበር፣ ሀገራዊ እድገትና ልማት በሰላም እንዲቀጥል የሚያስፈልገውን ምቹ ሁኔታ ለማስጠበቅ በሚደረገው ተጋድሎም ይገለጻል።

ዛሬ የጽናት ቀንን ስናከብር፣ የትናንቱን ጀግንነት ብቻ አንዘክርም። የነገዋን ኢትዮጵያ በጽናት፣ በአንድነት፣ በሰላምና በሀገር ፍቅር ለመገንባት ያለብንን የጋራ አደራ እናድሳለን። ምክንያቱም ሀገር በአንድ ትውልድ ብቻ አትገነባም፤ በትውልድ ትውልድ በሚተላለፍ አደራ ትጠነክራለች።

የትናንቱ ጀግንነት የዛሬ ብርታታችን ነው፤ የዛሬው ጽናት የነገው ተስፋችን ነው፤ የነገው ተስፋ ደግሞ የኢትዮጵያ ዘላለማዊ ጉዞ ነው።

ጀግናው ሠራዊታችን ቃሉን ያድሳል፤ ለቃሉ ይታመናል። በቃል ኪዳኑ ይፀናል፤ ሀገርንም አፅንቶ ወደ ከፍታዋ ያሻግራል።

በይታያል ምህረት

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት
https://dfmc.mod.gov.et/

https://youtube.com/@fdredefenseforce-9629?si=Av-sDKCopw1FfTW2

https://t.me/+E_EOiTY9eq85ODI0

https://www.facebook.com/fdredefense.official
❤37👍13🔥3🙏3🏆3👎1👏1
September 7, 2026 4K 4