የሀገር ኩራት የህዝብ መከታ የሆነ ሠራዊት
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ነሃሴ 30 ቀን 2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያ ለወታደር ከምንምና ከማንም በፊት ፣ የትምና መቼም ፣ ከድሮ እስከ ዘንድሮ ፣ ከትላንት እስከ ዛሬ ፣ ነገም ከነገ ወዲያ እስከ እድሜው ፍፃሜ ድረስ አቻ የማይገኝላት ተቀዳሚ ጉዳዩ ናት።
እንኳንስ ከሌላው ከራሱ ጋር አወዳድሮ የሚያስበልጠው እሷን ነው። እድሜ ዘመኑን በጀግንነት አገልግሏት ፣ አጥፊዋን ለማጥፋት ህይወትና አካሉን ገብሮላት ፣ እኔ ለሃገሬ ምን ሰራሁ እንጅ ሃገሬ ለኔ ምን ሰራችልኝ የማይላት እውነተኛ ወዳጇ ነው።
ከአንደበቱ የማይነጥላት የዘወትር መዝሙሩ ፣ ከራሱ በላይ የሚያልቃት የዜግነት ክብሩ ፣የዘላለም ፍቅሩ ፣ ደሙን አፍስሶ የሚታደጋት፣ ህይወቱን ከፍሎ የሚያስቀጥላት ፣ ኢትዮጵያ ማለት ለወታደር ሁለንተናው ናት።
ታዲያ ይህን ጥልቅ የሃገር ፍቅር ስሜቱን በውል የተረዱ ፣ ለቆመለት አላማ ያለውን ፅናት ጠንቅቀው የሚያውቁ ፣ ለሰላም ሲል የሚከፍለውን የማይተመን ዋጋ በሚገባ ያስተዋሉ ፣ ሃገር የሚያገለግልበትን አስተሳሰብ በአግባቡ የተገነዘቡና ከህዝብ አብራክ ወጥቶ ለህዝብ የመቆመ ሃይል መሆኑ የገባቸው ዜጎች ወታደርን የሚጠሩት የኔ ብለው ነው።
ከዚህም የተነሳ ወታደሩ የሃገርን ሰላም ለማረጋግጥ የሚደክመውን ያህል ዜጎች ለሰራዊቱ ደህንነት ይጨነቃሉ። ምንጊዜም ግዳጅ ወስዶ ሲሰማራ ሃገር ወዳዶች በሃሳብ አብረውት ይዘምታሉ።
ባላንጣዎቹን ፊት ለፊት ተጋፍጦ ሁኔታን በብቃት ለመሻገር ሲፋለም ፤ የእናቶች ፀሎት ፣ የአባቶች ምርቃት ፣ የወጣቶች እገዛ ተለይቶት አያውቅም። እሱም አንዱ የድል አድራጊነቱ ሚስጥር ይህ እንደሆነ ያምናል!
የኢትዮጵያ ወታደር ህዝብና ሃገሩን ከራሱ አስቀድሞ በመመልከት ፣ ጠላቱን አምርሮ የጠላበትን ፣ ትውልዱን አብዝቶ የወደደበትን ፣ ነፍሱን እስከ መስጠት የታመነበትን፣ የአላማ ፅናት ጠንቅቆ ያወቀ ማህበረሰብ ሁሌም የሚመለከተው በእኔነት ስሜት ነው።
የኢትዮጵያ ወታደር ዳር ድንበሩን በአጥንቱ ፍላፃ የማገረ ፣ የሃገሩን ሉአላዊ ክብር በጀግንነት ያፀና ፣ አስተማማኝ መሰረት ሆኖ ኢትዮጵያን ያቆመ የማዕዘን መሠረት ነው። ይህን እውነት ለመረዳት ደግሞም ትውልድን ጠብቆ ያስቀጠለ የታሪክ ባለ አደራ ፣ የአርበኞችን ፈለግ ተከትሎ የጀገነ የቁርጥ ቀን ደራሽ ፣ ጠላቶቿን አምርሮ የጠላ የሃገር ባለውለታ ፣ አይበገሬነቱን በዘመናት ተጋድሎ በተግባር ያረጋገጠ የወንዶች ቁና ፣ አያሌ ጊዜ ተፈትኖ ሁኔታን በድል የቋጨ የአሸናፊነት ናሙና ነው። የኢትዮጵያ ወታደር ።
ፈተናውን ከፊት ሆኖ የሚጋፈጥ የህዝብ አልኝታና መከታ ፣ ፀረ-ሰልሞችን ታግሎ በማንበርከክ ለተጨቆኑት ነፃነትን የሚያውጅ የምስኪኖች ዋስትና ፣ በአለም ዙሪያ ሁሉ ለሰው ዘር በሙሉ ሰላም ይሁን በሚል ሃገራዊ ጥንተ ዜማ የተቀኘ የሰላም አምባሳደር ፣ ሊሰራ ሲነሳ አድማስ የማይጋርደው ወሰን አልባ የሰው ልጆች ብሩህ ተስፋ ነው።
በኤፍሬም አድማሱ
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት
https://dfmc.mod.gov.et/
https://youtube.com/@fdredefenseforce-9629?si=Av-sDKCopw1FfTW2
https://t.me/+E_EOiTY9eq85ODI0
https://www.facebook.com/fdredefense.official
26
11
6
1September 5, 2026 3.5K 2