ጤና ይስጥልን ጥቂት ሥለጤናዎ ፦ የቲቢ በሽታ ምንድን ነው? የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ነሃሴ 24 ቀን 2018… — FDRE Defense Force - የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት — TG.ME

ጤና ይስጥልን ጥቂት ሥለጤናዎ ፦ የቲቢ በሽታ ምንድን ነው?

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ነሃሴ 24 ቀን 2018 ዓ.ም

* የቲቢ በሽታ ምንድን ነው?
ቲቢ ተላላፊ በሽታ ሲሆን  በባህሪው ቀስ በቀስ እያለ እያደገ የሚሄድ በመሆኑ ድንገተኛና አጣዳፊ ከሚባሉት የበሽታ ዓይነቶች ክፍል የሚመደብ አይደለም፡፡ የቲቢ በሽታ መንስኤም በዓይን የማይታይ ረቂቅ ተህዋስ ወይም ጀርም  ነው፡፡

* የቲቢ በሽታ ሥርጭትና ተጽዕኖዎች፡
የቲቢ በሽታ በዋናነት የሚተላለፈው በሳንባ ቲቢ የተጠቃና ሕክምና ያልወሰደ በተለይም በአክታ ምርመራ የቲቢ በሽታ አምጪ ባክቴሪያ የተገኘበት ሕመምተኛ ሲስል፣ ሲያነጥስ፣ ሲነጋገር ወዘተ... የበሽታው አምጪ የሆነው ጀርም ከታማሚው ሳንባ ውስጥ በመውጣት በቀጥታ በትንፋሽ ወይም በአየር አማካይነት ወደ ሌላ ሰው የመተንፈሻ አካል ሲገባ ነው፡፡
• በሽታው አልፎ አልፎ ማይኮባክቴሪየም ቦቪስ ተብሎ በሚጠራ ጀርም አማካኝነት በበሽታው ከተያዙ የቤት እንስሳት የሚገኝ ወተት ሳይፈላ ከተጠጣ ወደ ሰው ሊተላለፍ ይችላል፡፡

* የቲቢ በሽታ ምልክቶች
የቲቢ በሽታ ምልክቶች እንደተጠቃው የሰውነት ክፍል ይለያያል፡፡ በሽታው በአብዛኛው የሚያጠቃው ሳንባን  ስለሆነ የበሽታው ዋና ምልክት ሁለት ሳምንትና ከዚያ በላይ ለሆነ ጊዜ የዘለቀ ሳል ነው፡፡ ሳሉ አክታ ያለውና ደም የቀላቀለ ወይም ያልቀላቀለ ወይም ደረቅ ሊሆን ይችላል፡፡

ታማሚው ከሳሉ ሌላ በደረቱ አካባቢ የውጋት ስሜት፣መጠነኛ የሆነ ትኩሳት፣ ሌሊት በመኝታ ጊዜ ማላብ፣ የክብደት መቀነስ፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስና የሰውነት መድከም የመሳሰሉ አጠቃላይ የሆኑ ምልክቶች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ ከሳንባ ውጪ ያለ የቲቢ በሽታ ምልክቶች እንደተጠቃው የሰውነት ክፍል ዓይነት ይለያያሉ፡፡

* የቲቢ በሽታ ሕክምና
ቲቢ ዘመናዊና ፈዋሽ የሆኑ መድኃኒቶች አሉት፡፡ ይሁንና የቲቢ መድኃኒቶች በዋጋ ደረጃ ውድ በመሆናቸውና አብዛኛዎቹም ታማሚዎች ከፍለው ለመታከም ስለሚቸገሩ መንግሥት ለሁሉም የቲቢ ሕሙማን ከፍተኛ የመፈወስ አቅም ያላቸውን መድኃኒቶች በነፃ እንዲያገኙ አድርጓል፡፡

የቲቢ ሕመምተኛ የታዘዘለትን መድኃኒት ሳያቋርጥ ሙሉ በሙሉ መውሰድ ይጠበቅበታል፡፡ ለዚህም ሲባል መድኃኒት በአግባቡ ተወስዶ እስኪጠናቀቅ ድረስ ታካሚዎች በሚመርጧቸው የቲቢ ሕሙማን ደጋፊዎች የቅርብ ክትትል እንዲወስዱ ይደረጋል፡፡ ሕክምናው ከተቋረጠ ግን በሽታው በፊት ከነበረው ሁኔታ ከመባባሱም በላይ የበሽታ መንስኤ የፀረ-ቲቢን መድኃኒቶችን በመላመድ በመደበኛው  የቲቢ ሕክምና ዘዴ መፈወስ  የማይችል የቲቢ ዓይነት ይፈጠራል፡፡

* የቲቢ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር
የታዘዙ መድኃኒቶችን ባለማቋረጥ ወስዶ መጨረስና በሕክምናው መጨረሻ ላይ መፈወሱን ማረጋገጥ፣
ሰዎች በተሰበሰቡበት ቦታ ሲስሉም ሆነ ሲያስነጥሱ አፍና አፍንጫዋን በጨርቅ ወይም በመሃረብ በመሸፈን የበሽታው አምጪ ተህዋስያን እንዳይሠራጩ ማድረግ፣
አክታን በየቦታው ከመትፋት ይልቅ ክዳን ባለው ዕቃ ውስጥ ተፍቶ በመቅበር ወይም በማቃጠል የቲቢ በሽታ አምጪ ተህዋስያን እንዳይሰራጩ ማድረግ፣
የቲቢ ሕመምተኛ አብረው የሚኖሩ የቤተሰብ አባላትን፣ ሌሎች የቅርብ ግንኙነት ያላቸው ጉረቤቶችንና የሥራ ባልደረቦችን ሁሉ እንዲመረመሩ ማድረግ፣
የመኝታ ቤት መስኮቶችን በመክፈት በቂ የአየር ዝውውር እንዲኖርና የፀሐይ ብርሃንም እንዲገባ ማድረግ፤
በተቻለ መጠን ገንቢና ተመጣጣኝ የሆነ ምግብ መመገብ፣ ሲጋራ ከማጨስና ከአልኮል  መጠጦች መራቅ፣

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት
https://dfmc.mod.gov.et/

https://youtube.com/@fdredefenseforce-9629?si=Av-sDKCopw1FfTW2

https://t.me/+E_EOiTY9eq85ODI0

https://www.facebook.com/fdredefense.official
❤27👍10👏2
August 30, 2026 4.2K