✍️ ~ተፃፍዉ በ #RN05 ✍️
.
ህወሃት ከፋኖና ከኦላ ጋር ተጣምሮ እንቅስቃሴ መጀመሩን አውጇል። ይሄንንም ተከትሎ በኢትዮጵያ ፖለቲካ መነቃቃት መታየት ጀምሯል። ጥምረቱን አንዳዶች ሲያወድሱት የብልጽግና ካድሬዎች ደግሞ እያጣጣሉት ነው። ሌሎች ደግሞ ጥምረቱ ያሉበትን ችግሮች በመጠቆም ችግሮቹ ሳይፈቱ የሚደረግ የይድረስ ይድረስ ጥምረት ኋላ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ በመተበይ ጥምረቱ በጥንቃቄ እንዲታይ ሲያሳስቡ ይደመጣሉ። በሃገራችን ፖለቲካ በተደጋጋሚ እንደታዘብነው በጭፍን መደገፍ ወይንም በጭፍን መቃወም ካልሆነ በስተቀር ነገሮችን ከስሜት በራቀ መልኩ ተጨባጩን መተንተን በአንዱ ወይንም በሌላ ወገን አቀንቃኝነት ሲያስፈርጅም እያየን ነው።
.
ህወሃት፣ ፋኖና ኦላ በአንድ ወቅት በጠላትነት ተፈራርጀው በምላስና በነፍጥ ያለ ምህረት እርስ በርስ ሲጨፋጨፉ የነበሩ ከመሆናቸውም በላይ የአብይን የብልጽግና መንግሥት ከመገርሰ በዘለለ ምንም አይነት የጋራ የሆነ ራእይ የሌላቸው አማጽያን በመሆናቸው አሁን ደርሰው እየተጣመሩ መሆናቸውን ሲገልጹ ጥምረቱን ትኩረት ሰጥቶ መገምገም ተገቢ ብቻ ሳይሆን ግዴታም ነው ባይ ነኝ። እነኝህ አማጽያን ወገኖች እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ እርስ በርስ ሲዋጉ የነበሩ ብቻ ሳይሆን ነፍጥ ላማዘዟቸው ጉዳዮች እልባት ሳይሰጡ፣ እርዮቶቻቸውን ሳያጣጥሙና የጋራ የሆነ ራእይ ሳይኖራቸው ህብረታቸውን በአብይ መንግሥት ላይ ባላቸው ጥላቻ ላይ ብቻ መስርተው የሚፈጥሩት የጋራ ትግል ውጤታማ የመሆን እድሉ ላይ ብቻ ሳይሆን በለስ ቀንቷቸው የአብይን መንግሥት ቢገርሡ እንኳን ሃገሪቱ ሊገጥማት ስለሚችለው እድልና አደጋ መነጋገር ጨለምተኝነት ሳይሆን የሃላፊነት ስሜት ማሳያ ነው።
..
ሶስቱም ከመንግሥት ጋር ተፋላሚ ወገኖች የእየብሄሮቻቸውን ጥቅም ማስከበርን ተቀዳሚ አላማቸው አድርገው የሚንቀሳቀሱ እንደሆነ ይታወቃል። ፋኖን እንደምሣሌ ብንወስድ በግልጽ የአማራንና የኦርቶዶክስን የበላይነት ለማስመለስ እንደሆነ ነፍጥ ያነገበው በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲገልጽ ቆይቷል። እንደሚታወቀው ደግሞ ኢትዮጵያ የበርካታ ብሄር ብሄረሰቦችና ሃይማኖቶች አገር ናት። ታድያ ይህን የመሰለውን የኮሎንያል ፖለቲካዊ ትርክት አንግቦ ከሚንቀሳቀስ ቀኝ አክራሪ አማፂ ጋር የሚፈጠር ጥምረት ሌሎች ህዝቦች ላይ የስጋት ስሜትን መጫሩ ተፈጥሮዋዊ ነው።
.
ብዙዎች ለአማፅያኑ አለመግባባት ዋናው እንቅፋት ሊሆን የሚችለው ጉዳይ የወልቃይትና የራያ ይገባኛል ጥያቄ እንደሆነ አድርገው አስተያየት ሲሰጡ ይደመጣሉ። ለእኔ ግን ችግሩ ከወልቃይትና ራያ በጣም የገዘፈ እንደሆነ ነው የሚሰማኝ። ፋኖ ልክ እንደ ነገሥታቱ ዘመን መላዋን ኢትዮጵያ ጠቅልሎ ለመግዛት ነው እያለመ ያለው። ይህ ህልሙ ደግሞ ሃገሪቱን ወደለየለት የእርስ በርስ እልቂት እንዳይወስዳት ከተፈለገ ገና ከአሁን አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ህዝብ አምኖ መቀበል ይኖርበታል። ፋኖ ገና ለገና ለታክቲክ ብሎ ከቀድሞ ደመኞቹ ጋር ጥምረት ፈጠርኩ ስላለ ብቻ አመኔታ ሊሰጠው አይችልም። ይልቅስ ህልሙን/ቅዠቱን መሬት ላይ ለማውረድ መሞከር ሳይሆን እንዳያስበው እንኳን መንገዱ ከአሁን መዘጋቱን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው።
.
እርግጥ ነው አማፅያኑ አንዳንድ ያሉባቸውን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል ቀመር እንዳዘጋጁና በቀመሩም ላይ እንደተስማሙ ሲገልጽ ይደመጣል፤ ነገር ግን ቀመሩ ምን እንደሚመስል ለህዝብ እይታ የቀረበ ነገር የለም። የህዝብን አመኔታ ማግኘት ካስፈለግ ደግሞ አማጽያኑ የተስማሙባቸውን ጉዳዮች ለህዝብ አቅርበው ህዝብ አስተያየት ሊሰጥባቸው ይገባል።ይሄ ጉዳይ የፖለቲካ እንጂ ወታደራዊ ጉዳይ ስላልሆነ በሚስጢር የሚያዝበት ምንም ምክንያት የለም። ስምምነት ካለ የስምምነቱ ጭብጥ ለህዝብ ይፋ ሊሆን ይገባል። አለበለዚያ ግን ኋላ ላይ “አለባብሰው ቢያርሱ” የሚለውን ተረት የመተረት እጣ ላያችን ላይ ሊወድቅ ይችላል የሚል ስጋት አለኝ።
የእናንተስ ሃሳብ ምን ይመስላል?? ?
የእናንተን እይታ በኮመንት መስጫው ላይ አጋሩን!
.
.
.
ለተጨማሪ መረጃዎች የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ
📌 t.me/Fastsinfo99
🌴 🌴 🌴
