አሳዛኝ ዜና‼️
📍ከአድስ አበባ ወደ ደሴ ሲጓዝ የነበረ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ በሸኖ ከተማ አቅራቢያ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ6 ሰዎች ሕይወት አልፏል! 18 የሚደርሱ ቆስለዋል።
ሸኖ — በሸኖ ከተማ አስተዳደር ኦንቱ ቀበሌ፣ «አዳ ሀሮ» ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በደረሰ ከባድ የትራፊክ አደጋ የስድስት ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ፣ በ18 ሰዎች ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት መድረሱን የአካባቢው የትራፊክ ደህንነት ክፍሎች አስታወቁ።
የሸኖ ከተማ አስተዳደር የትራፊክ ደህንነት ማረጋገጫ ክፍል ኃላፊ ረዳት ኢንስፔክተር አብዲሳ መርጋ እንደገለጹት አደጋው የደረሰው የሰሌዳ ቁጥሩ 3-A04933 አ.አ የሆነ ‘ባስ ኤፍኤም’ የህዝብ ማጓጓዣ ተሽከርካሪ ከሚፈቀደው የፍጥነት ወሰን በላይ በማሽከርከሩ ምክንያት ነው ብለዋል።
በአደጋው ሕይወታቸው ካለፉት 6 ሰዎች መካከል 2 ወንዶች እና 4 ሴቶች እንደሚገኙበት ታውቋል።
በተጨማሪም ጉዳት ከደረሰባቸው 18 ተጓዦች (12 ወንዶች እና 6 ሴቶች) ውስጥ 13ቱ ከባድ እና መካከለኛ አደጋ የገጠማቸው ሲሆን፣ አምስቱ ደግሞ ቀላል ጉዳት አስተናግደዋል።
የሟቾች አስከሬን በህብረተሰቡና በትራፊክ ፖሊስ አባላት ትብብር ወደ ሸኖ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የተወሰደ ሲሆን፣ ተጎጂዎችም በዚሁ ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ይገኛል።
ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ተሳፋሪዎች ለተሻለ ህክምና ወደ ሌሎች ከፍተኛ ሆስፒታሎች የተላኩ ሲሆን፣ አነስተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ደግሞ ጉዟቸውን ወደ ደብረ ብርሃን እና አዲስ አበባ መቀጠላቸው ተገልጿል።


















