የገደል መንገድ ━━✦━━ ያ ደግ ሰው በመንደሩ ውስጥ እየተዘዋወረ ሳለ፣ ወጣት ወንድና ሴት ከዛፍ ሥር ቁጭ… — ከስነ-ፅሁፍ ዓለም — TG.ME

የገደል መንገድ
━━✦━━

ያ ደግ ሰው በመንደሩ ውስጥ እየተዘዋወረ ሳለ፣ ወጣት ወንድና ሴት ከዛፍ ሥር ቁጭ ብለው ሲጫወቱ ተመለከታቸው። የሚያወሩት ነገር ከስሜት የተሠራ ስለኾነ የሰሚን ጆሮ ከሩቁ ጠልፎ ያመጣል። እንደ ሰንደል ሽታ በአየር ላይ የቃጫ ገመድ መስሎ ይጥመለመላል፣ ይፈታል፣ ይዘረዘራል። ሰሚ ጆሮ ቃል እያሸተተ ርምጃውን ያሳድጋል፤ ሩቅ ከነበረበት "ምንድር ነው? ምንድር ነው?" እያለ ይጠጋል።

ያ ደግ ሰው ተጠጋ። በስሜት የታጀለ ንግግር ከወንዱ ወደ ሴቷ ይፈሳል። «አንቺና እኔ ጥቁር ምንጣፍ በመሰለ ጨለማ ላይ ብንንከባለል ጨለማው ርኩሰት የሌለበት ነጭ ሻሽ ነው የሚኾነው። ፍቅር የነገሠበት ቦታ ላይ ኹሉ ጽድቅ እንጂ ኩነኔ አይበቅልም» ይላታል። ሌላም ሌላም እያከለ ...

ያ ደግ ሰው "ሰው አለ" ብሎ ለማሳወቅ ጒረሮውን ሲጠርግ፣ ኹለቱም ብርግግ ብለው ቆሙ። ሴቷም ቸኮል ብላ ተሰናብታ ኼደች።

ያ ደግ ሰው፡ «እስኪ ና የኔ ልጅ! ትንሽ እንጫወት» አለው። ያ ልዝብ ቃል ይጥል የነበረው ወጣት እንደ ማፈር ብሎ ተጠጋው።

«ካለየኸኝ ቦታ ኾኜ ስታወራ የነበረውን ነገር ሰምቻለኹ። እንኳን ኹለት እግር ያለውን ሰው አራት እግር ያለውን ፍጡር ያንሸራትታል። እውነት ይህች ልጅ ላንተ በትልቁ መዝገብ የተጻፈችልህ ከኾነ መደበቅም፣ መንሾካሾክም አያስፈልግህም። በሰው ፊት ጮክ ብለህ ትጠራታለህ። ያለ ጊዜው ነገርን ቢቆርጡት ግን ዘር ኾኖ አይነሣም።»

«በምላስ ያልተወደደ ፍሬ አረም እንደሚባል፣ ከሰው ምላስ አትዋሉ። ተንጋዶ ያደገ ስሜት ፍሬው ዝሙት ይኾናል» አለው።

ያ ወጣት እጁን እያሻሸ መሬት መሬት እያየ ነበር።

ያ ደግ ሰው፡ «ቃልህ ግን ያምር ነበር - እንደ ፈሪ ወታደር ያለቦታህ እያፈሰስኸው ትጨርሰዋለህ እንጂ! ደሞ ትክክለኛዋ ሚስትህ ስትመጣ ምን ትላታለህ? ቀድመህ ቃልህን በትነኸው ተመልሰህ ልትሰበስበው ነውን?» አለው።
━━━━━━━━━
📔 ግርባብ - ያ ደግ ሰው
ፍቃዱ አየልኝ
📄 41 - 42
📖 📖 📖 📖 📖
https://t.me/Ethiobooks
Telegram
ከስነ-ፅሁፍ ዓለም
✍ አዝናኝ፣ አስተማሪና ቁም ነገር የሚያስጨብጡ የብዕር ውጤቶች የሚቀርቡበት የናንተው ቻናል! የቻናላችን https://t.me/Ethiobooks ቤተሰብ ሁኑ፣ ለወዳጅ ጓደኞቻችሁም 'share' አድርጉ። ለአስተያየት፣ ስነ-ፅሁፋዊ ጥቆማና ማስታወቂያ @firaolbm እና @tekletsadikK ተጠቀሙ።
👍6🤔2
August 5, 2026 1.5K 1