በኢፐሰዩ የአካዳሚክ ሰራተኞች የብቃት ምዘና መስፈርት ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተካሄደ በኢትዮጵያ… — Ethiopian Public Service University — TG.ME

በኢፐሰዩ የአካዳሚክ ሰራተኞች የብቃት ምዘና መስፈርት ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተካሄደ

በኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪሰ ዩኒቨርሲቲ (ኢፐሰዩ) የአካዳሚክ ሰራተኞች የብቃት ምዘና መስፈርት ላይ ነሀሴ 4 ቀን 2018 ዓ.ም በአባይ አዳራሽ የግንዛቤ ማስጨበጫ ገለጻ ተሰጠ። የቀረበው የምዘና መስፈርቱም በትምህርት ሚኒስቴር የጸደቀ ሲሆን፣ በመርሀ ግብሩ ላይም የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ሰራተኞች በሙሉ ተሳትፈዋል።

የምዘና መስፈርቱን አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት ዶ/ር ንጉስ ታደሰ ፣ ዩኒቨርሲቲው ባለፈው የትምህርት ዘመን በርካታና ሰፊ የለውጥ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸው፣ ከእነዚህም መካከል የነባር የትምህርት ፕሮግራሞችን መከለስና አዳዲስ ፕሮግራሞችን መቀረፅ ዋና እና በግንባር ቀደምትነት ውጤታማነቱ የተረጋገጠ ስራ መሆኑን አውስተዋል። አያይዘውም የምርምር አቅጣጫና አካሄድን ከተግባራዊ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲነት አንጻር የሚቃኝ የምርምር ፍኖተ ካርታ፣ እንዲሁም የስልጠናና ማማከር አገልግሎትን በሀገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ ደረጃውን የጠበቀ ለማድረግ የሚያስችል ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን ገልጸዋል። በተጨማሪም የአካዳሚክ ሴኔት ሌጅስሌሽን ክለሳና የተቋማዊ ጥራት ስታንዳርድ ሰነዶች ዝግጅት በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን እና የአዲሱን የተግባር ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ አደረጃጀት ማጥራትና የሰው ኃይል ልማትን ማጠናከር፣ የሀብት ማመንጫ ኢንተርፕራይዝ ማደራጀት፣ እንዲሁም ሁሉንም የዩኒቨርሲቲውን አገልግሎቶች በሂደት ዲጂታላይዝ ማድረግና ማዘመን ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ሥራዎች መከናወናቸውናና በቀጣይነትም እየተሰራባቸው መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በዚሁ የዩኒቨርሲቲውን አዲስ አደረጃጀት ማጥናትና የሰው ኃይል ምዘና ማካሄድን አስመልክቶ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንቱ በሰጡት ማብራርያ፣ ለዩኒቨርሲቲው በተግባር ሳይንስ ዩኒቨርሲቲነት የተዘጋጀው አዲስ መዋቅር አሁን ላይ በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በመታየት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ይህ የአደረጃጀት ጥናት እስከ ሰው ኃይል ትመና ድረስ የሚዘልቅ በመሆኑ፣ መምህራንን እና አመራሮችን በመዘን ወደ ሥራ ለማስገባት እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቁመዋል። የዚሁ የመምህራን እና አመራሮች የብቃት ምዘና የሕግ መነሻ የፌደራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 1353/2017 እና መመሪያ ቁጥር 1152/2011 ናቸው። የምዘናው ዋና ዓላማም የአካዳሚክ ሠራተኞችንና አመራሮችን በሳይንሳዊ መስፈርቶች መዝኖ ስምሪት መስጠት ሲሆን፣ በዚህም ጥራት ያለው ትምህርት፣ ምርምር፣ ሥልጠና፣ የማማከር አገልግሎት እና የማህበረሰብ ጉድኝት ሥራዎችን ውጤታማነት ማረጋገጥ እንደሆነ ተብራርቷል።

የምዘና መስፈርቱ ቴክኒካዊ ብቃት (62 በመቶ) እና ባህሪያዊ ብቃት (38 በመቶ) የተሰኙ ሁለት ዋና ዋና ክፍሎችን ያካተተ ሲሆን፣ አጠቃላይ ምዘናውም መምህራን በሚያቀርቡት ፖርትፎሊዮ፣ ሙያዊ አስተዋጽኦ እና ባህሪያዊ ብቃቶች ላይ ተመሥርቶ የሚካሄድ ነው። መመዘኛው እንደየአካዳሚክ ደረጃቸው (ከፕሮፌሰር፣ ተባባሪ ፕሮፌሰር፣ ረዳት ፕሮፌሰር እስከ ሌክቸረር) የተዘጋጀ ሲሆን በመማር-ማስተማር፣ በሥርዓተ-ትምህርትና ሥልጠና ፕሮግራሞች ክለሳና ቀረጻ፣ በሥራ አፈጻጸም ግምገማ፣ በሙያ ማሻሻያ ሥልጠናዎች፣ በምርምር ብቃት፣ በማህበረሰብ ጉድኝት፣ እንዲሁም ተቋማዊ አበርክቶና በኮሚቴ ተሳትፎ ዙሪያ የተዋቀሩ ዝርዝር መስፈርቶች ለታዳሚዎቹ ቀርበዋል። በተጨማሪም ባህሪያዊ ብቃቶች እንደየባህሪያቸው በየፈርጃቸው ተከፋፍለው በዝርዝር የቀረቡ ሲሆን፣ ምዘናው ሙሉ በሙሉ የዩኒቨርሲቲውን ዋና ዋና ተልዕኮዎች ታሳቢ ያደረገ፣ እያንዳንዱ አካዳሚክ ሠራተኛ ያለውን መረጃ አቅርቦ የሚመዘንበት እና ከአድልዎና ኢፍትሐዊነት የጸዳ መሆኑ ተብራርቷል።

ምዘናው የሚካሄደው ከዩኒቨርሲቲው ውጭ ባሉ ገለልተኛ አካላት በተዋቀረ ኮሚቴ አማካኝነት ሲሆን፣ በሂደቱ ላይ ሊነሱ የሚችሉ ቅሬታዎችን ለመፍታት የሚያስችል የአቀራረብና የአፈታት ሥርዓትም አብሮ ቀርቧል።
በመጨረሻም የቀረበው ሰነድ ለሁሉም የአካዳሚክ ሠራተኞች ተደራሽ እንደሚደረግ የተገለጸ ሲሆን፣ ከተሳታፊዎች ለተነሱ አስተያየቶችና ጥያቄዎችም በዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት ዶ/ር ንጉስ ታደሰ እና በአካዳሚክ ም/ል ፕሬዚደን ዶ/ር አማኑኤል ኩሲያ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
❤20🍌6
August 10, 2026 7.7K 11