በአባታችን ቄስ ተስፋ ጅሬን ዜና እረፍተ የተሰማንን ሀዘን እንገልጻለን።
* * ***
ቄስ ተስፋ ጅሬን ከልጅነታቸው አንስቶ በቤተ ክርስቲያኒያኒቱ ውስጥ ያደጉ፤ በቤተ ክርስቲያኒቱ ትምህርታቸውን የተከታተሉ እና ከዚያም በመምህርነት ህብረተሰባቸውን ያገለገሉ አባት ነበሩ።
ከቤተ ክርስቲያኒቱ ሙሉ ጊዜ ሰጥተው እንዲያገለግሉ በቀረበላቸው ጥሪ መሠረት፤ ከወንጌላዊነት አንስቶ በበርካታ እርከኖች እና ሃላፊነቶች ቤተ ክርስቲያንን አገልግለዋል። ቄስ ተስፋ የቅስና ሀላፊነት ተቀብለው ሙሉ የእረኝነት አገልግሎት መስጠት የጀመሩት በ1968 ዓ.ም በቦጂ ድርመጂ እናት ማህበረ ምዕመናን ነበር።
እስከ 1991 ዓ.ም በኖሌና ዴጌሮ ሰበካዎች የእግዚአብሔር ቃል በማስተማር እና ሰበካዎቹን በመምራት አገልግለዋል። ቀጥለውም 1991-1994 የምዕራብ ሲኖዶስ የወንጌል እና ቲኦሎጂ መምሪያ ዳይሬክተር፤ የቀድሞ የምዕራብ ሲኖዶስ ወደ አራት ሲኖዶስ ከተከፋፈለ በኋላ እንደ አዲስ በተዋቀረው የምዕራብ ሲኖዶስ ከ1994-2002 የመጀመሪያው ጠቅላይ ጸሐፊ ሆነው በትጋት እና በታማኝነት ቤተክርስቲያንን አገልግለዋል። በአገልግሎት ዘማናቸውም በሲኖዶሱም የሥነ መለኮት ኮሌጅ አስተምረዋል።
አባታችን ቄስ ተስፋ በጡረታ ከተገለሉም በኋላ በቤተ ክርስቲያኒቱ ህይወት እና አገልግሎት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የነበራቸው አባት ሲሆኑ የእረፍት ጊዜያቸውን በመጠቀም በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ <<BOOJJI KARKARROO IDDOO BARNOOTA AMMAYYAA FI WANGEELLI CAAFFATA AFAAN OROMOO ITTI JALQABE >> የተሰኘን ታሪካዊ መጽሐፍ በመጻፍ ለትውልድ አሻራ ጥለው አልፈዋል።
የቤተሰባቸውም ሁኔታ ባለ ትዳር እና የአራት ልጆች አባት ነበሩ።
ቄስ ተስፋ ጅሬን በተወለዱ በ80 ዓመታቸው ከዚህ አለም ድካም ያረፉ ሲሆን፤ የሽኝታቸውም ሥነ ሥርዓት በትውድ ሥፍራቸው ቦጂ ድርመጂ ቤተሰቦቻቸው፤ ወዳጅ ዘመዶች እና ከፍተኛ የሲኖዶሱ መሪዎች በተገኙበት ተካሂዷል።
የቤተ ክርስቲያኒቱም 22ኛ ካውንስል በዘመናቸው ስለ ሰጡት አገልግሎት ጌታን አመስግኖ ለቤተሰባቸውም መጽናናት ጸልዮአል።

















